ጀርመን ሁዋዌ እና ዜድቲኢ ስልኮችን ከ5ጂ ኔትወርክ ልታስወጣ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀርመን የቻይና ስሪት የሆኑትን ሁዋዌ እና ዜድቲኢ ስልኮችን ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት ከ5ጂ ኔትወርክ ልታስወጣ መሆኑን አስታወቀች፡፡
የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር÷ ውሳኔው የጀርመንን ኔትወርክ ስርዓት የተጠናከረ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።
ደህንነቱ የተጠበቀ እና የማይናወጥ የቴሌኮም መሰረት ልማት መገንባት እንደሚፈልግ ጠቅሰው÷ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል እንዲሁም ጀርመን በቻይና ላይ ያላትን የስልክ ጥገኝነት ለመቀነስ ውሳኔው አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ውሳኔውን ተከትሎ በሀገሪቱ ቮዳፎን፣ ዶች ቴሌኮም እና ቴሌፎኒካ የተባሉ የሞባይል ኦፕሬተሮች የቻይና ስሪት የሆኑትን ሁዋዌ እና ዜድቲኢ ስልኮችን ከ5ጂ ኔትወርክ ለማስወጣት መስማማታቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም እነዚህ ስልኮች እስከ 2029 ባለው ጊዜ ከመዳረሻ ኔትወርኮች፣ ከትራንስፖርት፣ ከመተላለፊያ መስመር እና ማሰራጫ 5ጂ ኔትወርኮች ላይ እንደሚወጡ ተመላክቷል፡፡
ሁዋዌ ኩባንያ በበኩሉ÷ የሁዋዌ ቴክኖሎጂ የሳይበር ስጋት ሊያስከትል እንደሚችል የሚያረጋግጥ መረጃ አለመኖሩን አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ኩባንያው እንደበፊቱ ከደንበኞች ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና በጀርመን ዲጂታላይዜሽንን ለማስፋፋት እና የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ መግለፁን ኤዢያ ኒውስ ኢንተርናሽናል ዘግቧል፡፡