Fana: At a Speed of Life!

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የብሪክስ ዓለም አቀፍ ትስስር ቴሌቪዥን ጣቢያ አባል ሆኖ እንዲሰራ ተመረጠ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ አባል ሆኖ መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምት ዛሬ ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እና የቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጃና ቶልስተኮቫ ተፈራርመዋል።

ጃና ቶልስተኮቫ በበይነ መረብ በተካሄደው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር÷ፋና የዓለም አቀፍ ቴሌቪዥን ጣቢያው አባል ሆኖ የተመረጠው በኢትዮጵያ ተመራጭ፣ ተደማጭ እና ተጽእኖ ፈጣሪ ሚዲያ በመሆኑ ነው ብለዋል።

አቶ አድማሱ ዳምጠውም በበኩላቸው÷ ፋና የብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ ቴሌቪዥን ጣቢያ አባል መሆኑ የብሪክስ አባል የሆነችው ኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም፣ ገጽታ እና ፍላጎት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያደርስ ያስችለዋል ብለዋል።

በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት ሁለቱ የመገናኛ ብዙሃን በይዘት፣ በቴክኖሎጂ እና በሰው ሃይል ስልጠና በትብብር እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ባለፈም የብሪክስ ቴሌቪዥን ጣቢያ የተመረጡ ይዘቶች በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቴሌቪዥን፣ ሬድዮ እና ዲጂታል ሚዲያ አውታሮች እንደሚሰራጩ ተጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተመረጡ ይዘቶች በብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ የመገናኛ አውታሮች እንደሚሰራጩ ነው የተመላከተው፡፡

መቀመጫውን ሩሲያ ያደረገው ዓለም አቀፉ የቴሌቪዥን ጣቢያ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ በአፍሪካ ከኬንያ፣ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሞዛምቢክ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር በትብብር ይሰራል፡፡

ከኢትዮጵያ ደግሞ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን በአጋርነት መርጧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.