በቀጣናው አስተማማኝ ሰላም የሰፈነው የጸጥታ ሃይሉና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው በመስራታቸው ነው – ጄኔራል አበባው ታደሠ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣናው አስተማማኝ ሰላም የሰፈነው የጸጥታ ሃይሉና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው በመስራታቸው ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሠ ገለጹ፡፡
ጄኔራል አበባው ታደሰ እና የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ የግዳጅ ቀጣናዎችንና በአካባቢው የተሰማሩ የጸጥታ ሃይሎችን ተመልክተዋል።
ጄኔራል አበባው በዚህ ወቅት÷በሶማሌ ክልል የሚነፍሰው የሰላም አየር ወደ ሌሎች ክልሎች ተንሰራፍቶ ኢትዮጵያ ወደ ልማት የምትሸጋገርበት ጊዜ እሩቅ አይደለም ብለዋል።
በአጠቃላይ በሠራዊቱ ብርቱ ተጋድሎ ቀጣናው ሰላሙ የተረጋገጠ እንዲሆን ምስራቅ ዕዝና የክልሉ ህዝብና ፖሊስ እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ የከፈሉት መስዋዕት በመሆኑ ሀገር ሁልጊዜም እንደምትኮራባቸው ተናግረዋል።
ጄኔራል መኮንኑ አልሸባብና የኢትዮጵያን እድገትና ብልፅግና የማይፈልጉ አካላት ተቀናጅተው በመስራት በርካታ ጊዜ የሽብር ተግባር ለመፈፀም ቢሞክሩም በሠራዊቱና በህዝቡ የነቃ ተሳትፎና ትግል ፍላጎታቸውን ማምከን ተችሏል ብለዋል።
በቀጣናው ትልቅ የሆነ ሀገርን መለወጥ የሚችል ስራ የሚሰራበት በመሆኑ የሰራተኞችን ደህንነት በማረጋገጥ ያለ ስጋት ስራቸውን እንዲሰሩ በማስቻል የፀጥታ ሃይሉ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ከፍተኛ ሚና እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።
የፀጥታ ሃይሉ ጥምር ኮሚቴ ሥራውን አጠናክሮ በመቀጠል ግዳጁ የተሳካ እንዲሆን ተልዕኮውን በሚገባ እየተወጣ ነው ማለታቸውንም ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በቀጣይም ሕዝቡን እንደ አንድ ኮሚቴ በመጠቀም በልማት ሥራው ተሳታፊ ማድረግ የጥምር ኮሚቴው ዋና ተግባር መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል።