ስፔንና ፈረንሳይ ተጠባቂ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ያደርጋሉ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ምሽት 4 ሠዓት ላይ ስፔን ከፈረንሳይ የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡
17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በጀርመን አስተጋጅነት እየተካሄደ ሲሆን÷ ዛሬ ስፔን ከፈረንሳይ 75 ሺህ 24 ተመልካች በሚያስተናግደው አሊያንዝ አሬና ስታዲየም የሚያድርጉት ጨዋታ የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ ስቧል።
ከፍተኛ ትንቅንቅ በታየበት የሩብ ፍጻሜው ጨዋታ ስፔን ጀርመንን 2 ለ1 በመርታት ለግማሽ ፍጻሜው ማለፏ ይታወሳል፡፡
እንዲሁም በመደበኛ እና በጭማሪ ሰዓት ከፖርቹጋል ጋር 0 ለ 0 የተለያየችው ፈረንሳይ በመለያ ምት አሸንፋ ነው ዛሬ ከስፔን ጋር ለምታደርገው ፍልሚያ የደረሰችው፡፡
ስፔንና ፈረንሳይ ለመጨረሻ ጊዜ በአውሮፓ ዋንጫ የተገናኙት ፖላንድና ዩክሬን እ.አ.አ በ2012 በጋራ ባዘጋጁት 14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ላይ ሲሆን በጨዋታው ስፔን ፈረንሳይን 2 ለ 0 በመርታት ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀሏ ይታወሳል።
ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም 36 ጊዜ ተገናኝተው ስፔን 16 ጊዜ በማሸነፍ ብልጫውን ስትወስድ፤ ፈረንሳይ ደግሞ 13 ጊዜ አሸንፋለች።
ቀሪ ሰባት ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።
የስፔኑ አሰልጣኝ ሉዊስ ዴ ላ ፉዌንቴ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ÷ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የራሱን አቀራረብ ይዞ የሚገባ ጠንካራ ተጋጣሚ በመሆኑ በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ ተናግረዋል፡፡
ለተመልካች የሚያዝናና ጨዋታ ከመጫወት በላይ የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ ወደሜዳ እንደሚገቡም አረጋግጠዋል፡፡
በፈረንሳይ በኩል የፊት መስመሩን አምበሉ ኪሊያን ምባፔ፣ ኮሎ ሙዋኒ እና ኦስማን ደምቤሌ ይመሩታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አማካዩ አደሪየን ራቢዮ ከቅጣት መልስ ለጨዋታ ዝግጁ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ቡድኑ ካደረጋቸው አምስቱ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ሁለቱን ሲሆን÷በሶስቱ አቻ ተለያይቷል፡፡
የፈረሳይ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዲዲየር ዴሾ በ12 ዓመታት ውስጥ በአውሮፓ ዋንጫ ጥሩ ውጤታቸው በፈረንጆቹ 2016 ራሷ ፈረንሳይ ባስተናገደችው መድረክ ለፍፃሜ ደርሳ በፖርቹጋል 1 ለ 0 ተሸንፋ ዋንጫውን ያጣችበት ነው፡፡