የአፍንጫ አለርጂ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰውነት ውስጥ የሚገኙ በሽታ ተከላካይ ህዋሶች ወደ ውስጥ ለሚገባ ባዕድ ነገሮች የሚሰጡት የመከላከል ምላሽ አለርጂ ይባላል፡፡
አለርጂ በአፍንጫ እና በሌሎች የመተንፈሻ አካላት ላይ ሊከሰት ይችላል፤ አንዳንድ የአለርጂ ህመሞችም ከባድ ህመም የሚያስከትሉ እና አጣዳፊ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ናቸው።
የአፍንጫ አለርጂ መነሻ ምክንያቶች ምንድናቸው?
ቅዝቃዜ፣ ሙቀት፣ አቧራ፣ ጭስ፣ ኬሚካሎች፣ መጥፎም ወይም ጥሩ ሽታና የወቅቶች መለዋወጥ የአፍንጫ አለርጂ መንስኤዎች ናቸው፡፡
ምልክቶቹም የአፍንጫ ፈሳሽ መዝረክረክ፣ ዐይን አካባቢ መብላት ወይም ማሳከክ፣ የአፍንጫ ማፈን እና ማስነጠስ፣ ንጹ ፈሳሽ ከአፍንጫ መውጣት፣ የአፍንጫ መድማት፣ ጉንፋን መሰል ምልክቶች በታማሚ ላይ የሚስተዋሉ ይሆናል፡፡
አለርጂውን ከሚቀሰቅሱ ማለትም አቧራ፣ ብናኝ ፣ ኬሚካሎች እና ሽቶዎች መጠንቀቅ ደግሞ የመከላከያ መንገዶች ናቸው፡፡
የህመሙ ምልክቶች የሚስተዋሉ ከሆነ ወደ ጤና ተቋማ በአፋጣኝ በመሄድ ህክምና ማድረግ እንደሚያስፈልግ ከዘውዲቱ ሆስፒታል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአፍንጫ አለርጂ ህክምና ምንድነው?
ለአለርጂው ከሚያጋልጡ ነገሮች መጠንቀቅ፣ አፍንጫን በውሃ እና በጨው ማጠብ፣ የአለርጂ መድሃኒቶች በኪኒን እንዲሁም በሀኪም ትዕዛዝ ተሰጥተው አፍንጫ ውስጥ በሚነፉ መድሃኒቶች ይታከማል፡፡