በትግራይ ክልል የነዳጅ ማደያዎች በዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት አገልግሎት እንዲሰጡ ሊደረግ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግ ተገለጸ።
የትግራይ ክልል የጊዜያዊ አስተዳደሩ የትራንስፖርትና መገናኛ ቢሮ፣ የጊዜያዊ አስተዳደር የንግድ ኤጀንሲ እና በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ሪጅን መግለጫውን ሰጥተዋል፡፡
በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የንግድ ኤጀንሲ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ብቃት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ክንደያ እንደገለጹት ፥ ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ነዳጅ የሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎችና ጀኔሬተር ባለቤቶች የነዳጅ ክፍያ ሥርዓት በቴሌ ብር እንዲገለገሉ ይሆናል።
ዘመናዊ አሰራሩ በክልሉ በሚገኙ 60 ነዳጅ ማደያዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆንም ነው ያስታወቁት።
የነዳጅ መቅዳትና የክፍያው ስርዓት ዘመናዊ የማድረግ ስራ ነዳጅ በጥቁር ገበያ እንዳይሸጥ ለመከለከልና የተሳለጥ አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም ፥ በነዳጅ አጠቃቀም ዙሪያ “የነበረው ሕገ ወጥ ሥራ ለግለሰቦች መበልፀገያ እንጂ ለህዝባችን የጠቀመ አይደለም” ብለዋል።
“ዘመናዊ የነዳጅ ግብይት አሰራር ተግባራዊ በማድረግ ህዝባችንን ተጠቃሚ እናደርጋለን” ያሉት ደግሞ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የትራንስፖርትና መገናኛ ቢሮ ኃላፊ አቶ ታደለ መንግስቱ ናቸው።
በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ሙሉ ወልደስላሰ በበኩላቸው ፥ ነዳጅ አሞላልና ክፍያ አፈፃፀም ላይ ያለው ኋላ ቀር አሰራር ተቀይሮ ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት በቴሌ ብር ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
መብራት የመጥፋትና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለመፍታት የሚያስችል ዝግጅት እንደተደረገ መግለጻቸውንም የዘገበው ኢዜአ ነው።