Fana: At a Speed of Life!

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ሀገር በቀል ችግኞች ይተከላሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ20 ሄክታር የደን ቦታ ላይ ሀገር በቀል ችግኞች እንደሚተከሉ የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የችግኞቹ ተከላ የሚካሄደው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት የደን መመናመንና መራቆት በሚታይባቸው በተለዩ የፓርኩ አካባቢዎች መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ወንዴ ተናግረዋል።

በዚህም ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የሀገር በቀል ችግኞችን በማፍላት የቦታ ልየታና የመትከያ ጉድጓድ ቁፋሮ ማካሄድ መቻሉን ገልጸዋል።

ግራር፣ ኮሶ፣ ወይራና ሌሎች ሀገር በቀል የደን ችግኞችን በስካውቶች፣ በአካባቢው ማህበረሰብና በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ሰራተኞች የጋራ ተሳትፎ በሐምሌ ወር እንደሚተከሉ አስታውቀዋል፡፡

የሚተከሉት ችግኞችም የፓርኩን የእጽዋት ብዝሃ ህይወት ለመጠበቅ እንደሚያግዙ አመልክተው÷ አስፈላጊው እንክብካቤና ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል ግብረ ሃይል ከወዲሁ መቋቋሙን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በፓርኩ ክልል በሚያዚያ ወር ተከስቶ በነበረው የእሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰበት የጓሳ ሳርና የደን ሃብት አሁን ላይ እየጣለ ባለው የክረምት ዝናብ ማገገም መጀመሩን ጠቁመው÷ የችግኝ ተከላው የፓርኩን ጥበቃ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

በበርካታ የብዝሃ ህይወት ሀብቱ የሚታወቀው የሰሜን ብሄራዊ ፓርክ ከ1 ሺህ 200 በላይ የእጽዋት ዝርያዎች እንደሚገኙበት የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.