Fana: At a Speed of Life!

ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ የሕዝብ እርካታን ለማሳደግ እየሠራን ነው-አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀት፣ ጊዜ እና የጥራት ደረጃ በማጠናቀቅ የሕዝብ እርካታን ለማሳደግ እየሠራን እንገኛለን ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድረ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት፣ በጥራትና በብዛት በማሳካት ቃላችንን በተግባር እያሳየን እንገኛለን ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች መሠረተ ልማት፣ የጤና አገልግሎት፣ ትምህርትና ቴክኖሎጂን በማስፋት ለአገር እድገትና ብልጽግና ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋልም ነው ያሉት።

“ካለፉት ሦስት ዓመታት የቀሰምናቸውን ልምዶች፣ ከአመቱ የቁጭት ዕቅድን ጋር በማዳበል ከፕሮጀክቶች ግንባታ ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እየፈታን የምንገኝ ሲሆን÷ በተያዘላቸው በጀት፣ ጊዜ እና የጥራት ደረጃ በማጠናቀቅ የሕዝብ እርካታን ለማሳደግ እየሠራን እንገኛለን” ብለዋል።

በተጨማሪም የፕሮጀክቶች ክትትልና አያያዝን በየጊዜው በከፍተኛ አመራር ደረጃ እየገመገምን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ቆይተናል።

በዚህም ከፕሮጀክቶቹ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮች ማለትም የገበያ ግሽበት፣ የምርምርና ዲዛይን፣ የግንባታ ግብአቶች አቅርቦት እና ከተቋራጮች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ሳይውሉ ሳያድሩ መፍትሄ መስጠት መቻሉንም ነው የገለፁት።

“ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከታታይ 11 ሺህ 1፣ 20 ሺህ70 እና 19 ሺህ 912 ፕሮጀክቶችን ያጠናቀቅን ሲሆን፤ በአጠቃላይ 50 ሺህ 983 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ ችለናል” ብለዋል።

በ2016 በጀት ዓመት በ 110 ነጥብ 91 ቢሊየን ብር እየተተገበሩ ካሉት 31ሺህ167 ፕሮጀክቶች ውስጥ 30 ሺህ 261 ፕሮጀክቶች (97 በመቶ) እንደ ክልል በእንቅስቃሴ ውስጥ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ከእነዚህ ውስጥ በ79 ነጥብ 43 ቢሊየን ብር ወጪ 20 ሺህ 664 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ዘንድሮ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል፤ ማለትም በ2016 ከታቀዱት አዳዲስ ፕሮጀክቶች ውስጥ 68 ነጥብ 3 በመቶ ተጠናቀዋል፤ ይህም ካለፉት ሦስት ዓመታት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል የሚያሳይ ነው ሲሉ ነው የገለፁት።

በዚህ የበጀት ዓመት ለምረቃ ከተዘጋጁት ውስጥ 7 ሺህ 636 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች በ61 ነጥብ 58 ቢሊየን ብር በመንግስት በጀት፣ 13 ሺህ 28 ፕሮጀክቶች በ17 ነጥብ 85 ቢሊየን ብር በዜግነት አገልግሎት መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡

ዘንድሮ በዜግነት አገልጎት ዘርፍ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ የተደረገው እንቅስቃሴ ካለፉት ሶስት አመታት ጋር ሲነጻጸር የላቀ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

በዚህም በትምህርት ዘርፍ የቡኡራ ቦሩ ትምህርት ቤቶችና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ፣ በጤናው ዘርፍ፣ የአዳዲስ ጤና ኬላዎች፣ ተጨማሪ የጤና ተቋማት፣ የማህበረሰብ ሞዴል ፋርማሲ እና በርካታ የእናቶች ማቆያዎች ግንባታ በዜግነት አገልጎት ተከናውነዋል።

ከውሃ አንፃር የምንጭ ማጎልበት፣ የቤተሰብ እና የማህበረሰብ ደረጃ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ እና የመጠጥ ውሃ መስመር ዝርጋታ በዜግነት አገልጎት ተከናውነዋል ነው ያሉት።

መንገዶችን በተመለከተ የአዳዲስ የቀበሌ ለቀበሌ አገናኝ የጠጠር መንገዶች ግንባታና ጥገና፣ የባህል/ትንንሽ ድልድይ ግንባታ፣ የውስጥ ለውስጥ አዳዲስ መንገዶች ግንባታ፣ ጥርብ ድንጋይ መንገዶች ዝርጋታ ተከናውነዋል ብለዋል አቶ ሽመልስ።

በተጨማሪም የጎርፍ ማፋሰሻ ዲች ግንባታ፣ የጥቃቅን እና አነስተኛ ሼዶች ግንባታ፣ የገበያ ማዕከላት ግንባታ፣ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት ግንባታ፣ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ግንባታ፣ የቀበሌ ጽሕፈት ቤቶች ግንባታ፣ ወዘተ በህዝባችን የዜግነት አገልጎት መሰራት መቻላቸውንም ነው ያነሱት፡፡

በዚህ አጋጣሚ በአጠቃላይ ፕሮጀክቶቻችን በተያዘላቸው ጊዜ፤ በጀትና ጥራት ማጠናቀቅ ተጨማሪ ወጪዎች በመቀነስ የህዝባችንን ህይወት በማሻሻል የክልላችንን፤ እንዲሁም የአገራችንን ኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ አዎንታዊ መሻሻልን የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።

እነዚህ አመላካቾች መንግስት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ያሳየውን ውጤታማ እቅድ፤ ተአማንነት እና ወደፊት ዕቅዶቹን ሳያዛንፍ ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን ገልጸው ለእስካሁኑ ስኬት መገኘት ህዝቡ ለተወጣው ኃላፊነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.