Fana: At a Speed of Life!

በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ጉዳዮች በዕርቅ እልባት ማግኘታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በአስማሚነት መር የዳኝነት አገልግሎት በ2016 በጀት ዓመት ብቻ ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ጉዳዮች በዕርቅ እልባት እንዲያገኙ መደረጉ ተገለጸ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ሌሊሴ ደሳለኝ እንደገለጹት÷ በበጀት ዓመቱ በአስማሚነት መር የዳኝነት አገልግሎት 5 ቢሊየን 116 ሚሊየን 698 ሺህ ብር ግምት ያላቸው ጉዳዮች በዕርቅ እልባት አግኝተዋል፡፡

በዕርቅ እልባት ለማግኘት አገልግሎቱን ጀምረው ባለመስማማት መዝገባቸው ወደ መደበኛ ችሎት እንዲሄድ የሚያደርጉ ባለጉዳዮች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በፍርድ ቤቱ በዚሁ ዓመት በጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር በኩል በበጀት ዓመቱ 800 የሚደርሱ መዛግብቶች በድህረ ፍርድ ኦዲት ሂደት ማለፋቸውን ገልጸው፤ ጥራት ያለው የተፋጠነ ፍትህ ለመስጠት የክትትል ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

አልፎ አልፎ የውሳኔ ጥራት ችግር እንደሚያጋጥም ጠቅሰው፤ የስነ-ስርዓት ህጉን ያልተከተሉ አቤቱታዎችን በማቅረብ የተፋጠነ ፍትህ እንዳይሰጥ እንቅፋት የሚሆኑ አቤቱታ የሚያቀርቡ ባለጉዳዮች መኖራቸውን አመልክተዋል።

አሁን ላይ በፍርድ ቤቱ የተጀመሩ ተደራሽነትን የማስፋፋት ስራዎች በሀዋሳ፣ ዲላ፣ ወላይታ፣ ቡታጅራ፣ ወራቤ፣ ወልቂጤ፣ ጂግጂጋ አርባምንጭ ከተሞች እንዲሁም በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በተዘዋዋሪ ችሎት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ ተጠቁሟል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.