በኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት የተከማቹ ቅሬታዎች ተፈትተዋል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብን ቅሬታ በመስማት የኢሚግሬሽን ስራ ማስተካከያ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠትና ተቋማዊ ለውጦችን በማከናወን በጥቂት ወራት ውስጥ ብዙ ማሻሻያዎች እየተተገበሩ ይገኛሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ለምሳሌ ያህልም በቀን በኦላይን 900 ፓስፖርት መስጠት የነበረውን አገልግሎት ወደ 1 ሺህ 700 ማድረስ መቻሉንና ቀደም ብለው የተጠራቀሙ ጥያቄዎችን አስተናግዶ ለመጨረስ በተሰራ ስራ 1 ሚሊየን ፓስፓርት ታትሞ ገብቶ እስከ 87 በመቶ መሰራጨቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ገልፀዋል፡፡
የተከማቹ ቅሬታዎች መቶ በመቶ ተፈትተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ በህገወጥ መንገድ የሚኖሩ 10 ሺህ 467 ሰዎችን መመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
ሃሰተኛ ማስረጃ የያዙ 18 ሺህ ሰዎች ቅጣት እንዲከፍሉ ተደርጓል፣ በ188 ሀገሮች የቪዛ አገልግሎት በመክፈት ለ819 ሺህ 278 ተስተናጋጆች e-visa ጨምሮ የቪዛ አገልግሎት ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡
እንዲሁም ለ4 ሚሊየን 276 ሺህ 474 ግለሰቦች በአየርና በየብስ መዳረሻ ጣቢያዎች አገልግሎት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ተቋሙን የዘመነ እና አገልግሎቱን በጥራት የሚሰጥ ተቋም ለማድረግ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ነው ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) የገለፁት፡፡