ሩሲያና ኢራን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ቃል ገቡ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ እና ኢራን በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ቃል ገብተዋል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በካዛኪስታን በተካሄደው የሻንጋይ የትብብር ድርጅት (ኤስሲኦ) ከኢራን እና ኳታር መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
ድርጅቱ የምዕራባውያንን ጥምረት ለመመከት በፈረንጆቹ 2001 በሩሲያ እና በቻይና የተቋቋመ ነው።
የኢራን ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት መሃመድ ሞክበርን ያነጋገሩት ፑቲን፥ የሩሲያ እና የኢራን የንግድ ግንኙነት በእጅጉ መሻሻሉን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን በወቅቱ፥ በሀገራቱ መካከል ያለው የቱሪዝም እድገት የጎላ መሆኑን በትኩረት መመልከታቸውም ነው የተነሳው፡፡
የኢራን ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት መሃመድ ሞክበር የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ መልእክትን አስተላልፈዋል ተብሏል፡፡
መልዕክቱ፥ የኢራን ሁለተኛ ዙር ምርጫ ውጤት ምንም ይሁን ምን ከሩሲያ ጋር ያለው ጠንካራ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚያነሳ ነው።
ፕሬዚዳንት ፑቲን ከስብሰባው ጎን ለጎን፥ የኳታር ኤሚር ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ሀገራቸው በሰብአዊ ጉዳዮች ላይ ከሩሲያና ዩክሬን ቀውስ ጋር ተያይዞ ለምታደርገው ጥረት ማመስገናቸውን የዘገበው አፍሪካ ኒውስ ነው።