Fana: At a Speed of Life!

የአከራይ ተከራይ ውል ምዝገባ ተራዘመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአከራይ ተከራይ ውል ምዝገባ እስከ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ መራዘሙን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው የመኖሪያ ቤት ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ 1320/2016 መውጣቱን ተከትሎ እንደ አዲስ አበባ ከተማ በአዋጁ ማስፈፀሚያ መመሪያ ቁጥር 7/2016 በማውጣት ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ ምዝገባ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ በሁሉም ክፍለ ከተማና ወረዳዎች የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

በዚህም ከሰኔ 1 እስከ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 248 ሺህ 469 የኪራይ ውል መመዝገቡን የገለፀው ቢሮው÷አሁንም ምዝገባው እንደቀጠለ አመላክቷል፡፡

በመሆኑም በርካታ ተመዝጋቢ በመኖሩ ምክንያት ቀኑ እንዲራዘም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄው በመነሳቱና ቀሪ ያልተመዘገበውን የተከራይ አከራይ ውል እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 መዝግቦ ለማጠናቀቅ አዳጋች እንደሆነ ተቋሙ መገንዘቡን ጠቁሟል፡፡

በጊዜ ገደቡ ሳይመዘገብ የሚቀር ውል እንዳይኖር ለማስቻል የምዝገባ ጊዜውን ማራዘም በማስፈለጉ የምዝገባ ጊዜው እስከ ሐምሌ 24 ቀን 2016ዓ.ም መራዘሙንም ነው ቢሮው የገለጸው፡፡

የግል መኖሪያ ቤት አከራይም ሆነ ተከራይ የሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ ጊዜያቸውን ተጠቅመው እንዲመዘገቡ ቢሮው በድጋሚ አሳስቧል።

የውል ምዝገባው ከመደበኛ የስራ ሰዓት ውጪ በምሽት፣ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ እንደሚካሄድም የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.