Fana: At a Speed of Life!

የታክስና ጉምሩክ ህግ-ተገዥነት ንቅናቄ ማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከየካቲት 2015 ዓ.ም እስከ የካቲት 2016 ዓ.ም የተካሄደው የታክስና ጉምሩክ ህግ-ተገዥነት ንቅናቄ ማጠቃለያ እና አዲስ ንቅናቄ ማስጀመሪያ ፕሮግራም እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሐ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ታማኝ ግብር ከፋዮች ተገኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባስተላለፉት መልዕክት “ታማኝ ግብር ከፋይ እንደ ዓድዋ ጀግና፤ ግብር የማይከፍልና የሚያጭበረብር ደግሞ እንደ ባንዳ መቆጠር አለበት” ብለዋል።

አክለውም፥ በጦርነት ጊዜ ከባዱን የደም ግብር ለሀገር በመክፈል ላቅ ያለ ታሪክ ያለው ኢትዮጵያዊ በሰላሙ ጊዜ ቀላሉን የገንዘብ ግብር ለመክፈል ደካማ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በራሳችን ግብር የራሳችንን ወጭ መሸፈን ላይ ገና ያላሸነፍነው ዓድዋ ነው በማለት ገልጸው፤ ጠንካራ የገቢ ስርዓት የገነቡ ሀገራት በየትኛውም መድረክ የተከበሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም ሁሉም ዜጋ በኃላፊነት ግብር የመክፈል ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ÷ የደንበኞችን አገልግሎት ለማቀላጠፍና ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ መሆኑንና ግብር ከፋዩን ከእንግልት ለማላቀቅ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመተግበር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም ለግብር አሰባሰብ ፈተና የሆኑ ጉዳዮችን ለመከላከል ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

“በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ህገ ወጦችን ብንይዝም ገና ያልደረስንባቸው ይበዛሉ፤ ለዚህም በቁርጠኝነት እንሰራለን” ብለዋል።

በታክስና ጉምሩክ ህግ-ተገዥነት ንቅናቄ ማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ለንቅናቄው መሳካት አስተዋጽዖ ላደረጉ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በገቢዎች ቢሮዎቻቸው በኩል እውቅና ተሰጥቷል።

በፍሬህይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.