Fana: At a Speed of Life!

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 36ኛ መደበኛ ጉባኤ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን አጽድቋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

አዋጁ ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ትልቅ ሚና ያለውና የካፒታል ዕቃዎችን ሳይጨምር በዕቃና አገልግሎት ፍጆታ ላይ የተጣለ ስለመሆኑ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ረገድ የተደረጉ ለውጦችን በተለይም የኤሌክትሮኒክስ ግብይትንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ አዳዲስ እሳቤዎችን በሀገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በማካተት ታክሱ ለኢኮኖሚው ዕድገት የሚፈለገውን እገዛ እንዲያደርግ ለማስቻል ያለመ አዋጅ ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡

አዋጁ በታክስ ከፋዩና በታክስ ሰብሳቢው መስሪያ ቤት መካከል ሲፈጠር የነበረውን ያለመግባባት በማስወገድ ምቹ የታክስ አስተዳደር እንዲኖር እንደሚያግዝም ነው የተመላከተው፡፡

መንግስት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሃብት ተገቢውን ድርሻ እንዲያገኝ የሚያስችልና ከታክስ ነፃ መብት ገደብ የሚያበጅ አዋጅ እንደሆ አቶ ደሳለኝ ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ አስረድተዋል፡፡

ምክር ቤቱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላም አዋጅ ቁጥር 1341/2016 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ባወጣው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ የወጪ ንግድ የቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት አዋጅ ላይ የተወሰነ ማሻሻያ በማድረግ አዋጅ ቁጥር 1342/2016 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

የማሻሻያ አዋጁ የዓለም አቀፍ ገበያ በመቀዛቀዙ ምክንያት ያመረቱትን ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ያልቻሉ አምራቾችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.