Fana: At a Speed of Life!

የሐረር ኢኮ ፓርክና የጅብ ትርዒት ማሳያ ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረር ኢኮ ፓርክ እና የጅብ ትርዒት ማሳያ ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡

ፓርኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሐረር የጅብ ማብያ ለቱሪስት ምቹ ሆኖ እንዲሰራ በሰጡት መመሪያ መሰረት ከመደመር ትውልድ መጽሐፍ ገቢና ከክልሉ መንግስት ከተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በም/ጠ/ሚ ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ÷የሐረር ኢኮ ፓርክ እና የጅብ ትርዒት ማሳያ ለሐረር ከተማ እጅግ አስፈላጊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

የፕሮጀክት ዲዛይን እና ግንባታው ከአካባቢው እና ተፈጥሮ ጋር በሚስማማ መልኩ የተከናወነ መሆኑን እንደታዘቡም አንስተዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ÷ ከመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ በተገኘ ገንዘብ የተገነባው የሐረር ኢኮ ፓርክ እና የጅብ ትርዒት ማሳያ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ በ210 ቀናት መጠናቀቁን ጠቁመው÷ ፕሮጀክቱ የስራ ባህልን ከመቀየሩ ባለፈ በቀጣይ ጊዜያት ለሚሰሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ፓርኩ ሐረር የምትታወቅበትን የጅብ ማብላት ትርዒት ማስቀጠል እና ሀገር በቀል ዕፅዋቶችን በስፋት ለማብቀል ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በሜሮን ሙሉጌታ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.