መንግስት ለሰላም ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ለሰላም የሚከፈል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡
በዚህም በሰላም ጉዳይ ላይ ባነሱት ሃሳብ እንዳሉት፥ መንግስት ከለውጡ ማግስት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥሪ ማቅረቡን አስታውሰው፥ ይህም ለሀገር ግንባታ ሁሉም የራሱን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዋልታ ረገጥ የሆነ እሳቤ ይቅር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እኔ ብቻ ሳይሆን እኛ በማለትና በመደመር በጋራ እንቀጥል ብለናል ነው ያሉት፡፡
ምንም ያህል ብንሰራ በብሔር የምንገፋፋ ከሆነ ትርጉም የለውም፤ ለዚህም መስከን ይገባል ብለዋል፡፡
ሰላም ማጣት በኢትዮጵያ ስር የሰደደ በሽታ ነው፤ ይህ እንዳይሸጋገርም በምክክር እናቁመው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግስት ጦርነት እንዳይከሰት ብዙ ዋጋ መክፈሉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፥ እንደአብነትም ከሸኔ፣ ከህወሓትና በተመሳሳይ ከአማራ ክልል ታጣቂዎች ጋር ለመነጋገርና ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የሄደበትን ርቀት አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለረዥም ዘመናት በግጭትና ጦርነት አዙሪት ውስጥ አልፋለች፤ ይህ የመገዳደል ታሪክ በእኛ ትውልድ ሊቆም ይገባል፤ መንግስት ለሰላም የሚከፈል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያትም መንግስት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ በሆደ ሰፊነት በርካታ ርቀት መጓዙን ጠቅሰው፥ በግጭትና ጦርነት ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን መያዝ ፈጽሞ አይቻልምም ሲሉ ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ዛሬም ነገም የሚበጀው በሰላምና በሰከነ መንገድ ተወያይቶ ችግሮችን መፍታት እንደሆነም ነው የጠቆሙት፡፡