Fana: At a Speed of Life!

ከለውጡ በኋላ ከ30 ሺህ በላይ ቅድመ መደበኛ ት/ቤቶች ተገንብተዋል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከለውጡ በኋላ ከ30 ሺህ በላይ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከም/ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መንግስት ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡

በዚህም ባለፉት ዓመታት ከ30 ሺህ በላይ ቅድመ መደበኛ (ኬጂ) ትምህርት ቤቶች መገንባቸውን አንስተዋል፡፡

ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ከሚከናወን ግንባታ ባሻገር የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎቶች እየተስፋፉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለትምህርት ሥርዓቱ አካታችነት ዘመናዊ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት መገንባቸውን ጠቅሰው ፥ ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

በአንጻሩ ለውጡን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲ አለመገንባቱን ጠቅሰው ፥ በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች ጥራትን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከለውጡ በፊት የዩኒቨርሲቲ በጀት የነበረው 40 ቢሊየን ገደማ እንደነበር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ፥ አሁን ላይ ግን 60 ቢሊየን ገደማ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ላይ በርካታ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.