Fana: At a Speed of Life!

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ ሲከናወንባቸው ለነበሩ 47 ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀስ ፀረ-ሰላም ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ ሲከናወንባቸው ለነበሩ 47 ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት ተፈቀደ።

እንዲሁም ሌሎች በቁጥጥር ውለው ምርመራ ሲከናወንባቸው በነበሩ 14 ተጠርጣሪዎች ላይ ለዐቃቤ ሕግ የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቅዷል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በአጠቃላይ በሦስት መዝገብ የተከፈሉ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ተመልክቷል።

በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀስ ፀረ-ሰላም ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በስራ ላይ በነበረበት ጊዜ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በምርመራ ላይ በቆዩ 47 ተጠርጣሪዎች ላይ ለሦስተኛ ጊዜ የፌደራል ፖሊስ መርማሪ 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ተጠርጣሪዎቹ ለ60 ቀናት በእስር ላይ እንደቆዩ ጠቅሰው፤ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ የደንበኞቻቸው የዋስ መብት እንዲከበር ጠይቀዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የመረመረው ችሎትም በተጠርጣሪዎቹ ላይ ፖሊስ በቂ ጊዜ እንዳለው ጠቅሶ በየደረጃው በ20 ሺህ እና በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ በፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ የ15 ቀን ክስ መመስረቻ የጠየቀባቸውን በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ የ14 ግለሰቦችን መዝገብ ተመልክቷል።

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ ሲጣራባቸው የቆዩ 14 ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ ምርመራ ማጠናቀቁንና የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡንም አስታውቋል።

ዐቃቤ ሕግም የምርመራ መዝገቡን ትናንት መረከቡን ጠቅሶ፤ በወ/መ/ስ/ህግ ቁጥር 109/1 መሰረት መዝገቡን ተመልክቶ መወሰን እንዲያስችለው የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆችም ዐቃቤ ሕግ ምርመራውን ከፖሊስ ጋር ሲመረምርና ሲመራ ቆይቶ እንደ አዲስ ክስ መመስረቻ ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱ ተገቢ አይደለም በማለት ደንበኞቻቸው የዋስ መብት እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

የግራ ቀኝ ክርክሩን የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱም ከተጠረጠሩበት ወንጀል አንጻር ክስ መመስረቻ ጊዜ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ለዐቃቤ ሕግ ፈቅዷል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር በእስር ሆነው ምርመራ ሲከናወንባቸው በነበሩት የፌደራል ማረሚያ ቤት ፖሊስ የቀድሞ አባላት እነ ኮንስታብል ልጅ አዲስ ወርቁ ጥበቡ መዝገብ ያሉ አራት ተጠርጣሪዎችን በተጠረጠሩበት የማረሚያ ቤት ንብረትን ይዞ መሰወር፣ በዕምነት ማጉደል ወንጀል ተነጥለው በሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ መመስረቻ ጊዜ ተጠይቆባቸው ክርክር ተደርጓል።

ፍርድ ቤቱም በእነዚህ አራት መዝገባቸው በተነጠሉ ተጠርጣሪዎች ላይ በዐቃቤ ሕግ ከቀረበ የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጥያቄ ውስጥ የ10 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ለዐቃቤ ሕግ ፈቅዷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.