በእነ ቀሲስ በላይ መኮንን መዝገብ ዐቃቤ ሕግ ምስክር አሰማ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአፍሪካ ኅብረት ሒሳብ 6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር የምዝበራ ሙከራ ጋር ተያይዞ በተከሰሱት በእነ ቀሲስ በላይ መኮንን መዝገብ ላይ ዐቃቤ ሕግ ምስክር አሰምቷል፡፡
የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ቃል የሰማው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በእነ ቄስ በላይ መኮንን፣ በግብርና ኢንቨስትመንት በተሰማራው ኢያሱ እንዳለ ወ/መስቀል፣ በኮሚሽን ስራ በተሰማራው በረከት ሙላቱ ጃፋር፣ ዓለምገና ሳሙኤል ዲንሳ እና የኒሞና ንግድ ስራ ኃላ/የተ/የግል ማኅበር ስራ አስኪያጅ አበራ መርጋ ተስፋዬ ላይ÷ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ ቁጥር 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 2 እና ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ እና በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ ቁጥር 382 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከአፍሪካ ኅብረት የክፍያ ትዕዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር ለተከሰሱ ግለሰቦች የተለያየ የዶላር መጠን ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የሚል አጠቃላይ የ6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ሀሰተኛ የክፍያ ሰነድ በአንደኛ ተከሳሽ መቅረቡን ጠቅሶ በሁሉም ግለሰቦች ላይ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ችሎት የቀረቡና የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን÷ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በአድራሻቸው ባለመገኘታቸውና በተደጋጋሚ ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ለጊዜው ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ችሎት የቀረቡት ተከሳሾችም ክሱ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ ክስ መቃወሚያ ነጥቦችን ፍርድ ቤቱ መርምሮ ወደፊት በማስረጃ እንደሚጣራ በማመላከት ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው፤ ተከሳሾቹ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎም ዐቃቤ ሕግ ዛሬ ሦስት ምስክሮችን አቅርቧል።
ቀረበ ስለተባለው የክፍያ ሰነድና ተያያዥ ጉዳዮችም የምስክር ጭብጥ በማስመዝገብ በዋና ጥያቄ የምስክሮቹን ቃል አሰምቷል።
የተከሳሽ ጠበቆችም መስቀለኛ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በፍርድ ቤቱ የማጣሪያ ጥያቄ ተነስቶ ከምስክሮች መልስ ተሰጥቶበታል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ምስክር ቃልን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ