Fana: At a Speed of Life!

ም/ቤቱ ነገ ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት የ2017 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የፌዴራል መንግስት የ2017 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ነገ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ ይካሂዳል፡፡

በኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 55 (17) እና በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 81 (3) እና አንቀፅ 92 መሰረት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደበኛ ስብሰባው በመገኘት በፌዴራል መንግስቱ የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 55 (11) እና በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 76 መሰረትም ምክር ቤቱ የ2017 የፌዴራል መንግስት በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን አስመልክቶ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ የሚያቀርበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አዳምጦ ረቂቅ በጀቱን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በምክር ቤቱ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.