የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለመቋቋም በትብብር መስራት እንደሚገባ ተመለከተ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየር ንብረት ለውጥን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ለመከላከልና ለመቋቋም የጋራ ጥረትና ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኦየስ ግሎባል ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት “ግሎባል ሲቲዝን ፕላስ 2024” የተሰኘው የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ጉባዔው በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላምና ግጭት አፈታት እንዲሁም በሌሎች በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ዛሬና ነገ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ የጤና ችግር፣ የምጣኔ ኃብት ድቀትና ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ እያስከተለ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ በመሻት የበለፀገችና ፍትሃዊነት የተረጋገጠባትን ዓለም ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የጋራ ጥረትና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ነድፋ እየሰራች መሆኑንም መጥቀሳቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ግሎባል ሲቲዝን ፕላስ 2024 ጉባዔም ለዚህ ውስብስብ ችግር የመፍትሔ ሃሳቦች የሚቀርብበት እንደሚሆን እምታቸውን ገልጸዋል።