ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በኡጋንዳ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በኡጋንዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ከኡጋንዳ ህዝብ መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሙሆዚ ኬይነሩጋባ በተደረገላቸው ግብዣ መሰረት ነው ጉብኝቱ እያደረጉ የሚገኙት።
በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራው ልዑክ ኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በኡጋንዳ ምድር ሃይል አዛዥ በሌ/ጄኔራል ኬያንጃ ሙሀንጋ፣ በኡጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር እፀገነት በዛብህ ይመኑና በሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል እንደተደረገላቸው ተገልጿል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሙሃዚ ኬይነሩጋባ ጋር በሀገራቱ በመከላከያ ዘርፍ ባላቸው ትብብር ዙሪያና የቀጠናውን ሰላምና ፀጥታ በማስፈን ረገድ እያደረጉት ያለውን ሚና አጠናክረው ለማስቀጠል በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
ውይይቱ በሀገራቱ መካከል ያለውንና ዘመናትን የተሻገረውን የሁለትዮሽ ግንኙነትና ወዳጅነት በማጠናከር በርካታ የጋራ ውጤቶችና ጥቅሞችን በማስገኘት አሁን ያለበትንም ሁኔታ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር እንደሚታመን ተጠቁሟል።
ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት በአሁኑ ወቅትም ተጠናክሮ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከመከላከያ ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ከኡጋንዳ ጋር ያላት ግንኙነት ስትራቴጂክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከተጠናከረው የሁለትዮሽ ግንኙነት በተጨማሪ በቀጠናው ሰላምና ጸጥታን በማስፈን ረገድ ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በውይይቱ ሁለቱ ሀገራት በተናጠልም ሆነ በጋራ የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የተሻለ አስተዋፅዖ ለማበርከት የሚቻልበት ሁኔታን የዳሰሰ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
በአቅም ግንባታና ተጨማሪ ትብብሮችን አስመልክቶ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ለማድረግ ትኩረት ሰጥተው ከስምምነት ላይ ደርሰዋል ነው የተባለው፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በነገው ዕለት ከኡጋንዳ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ ይጠበቃል።