Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ 5 የዩክሬን SU-27 ተዋጊ ጄቶችን ማውደሟን አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በዩክሬን ላይ በሰነዘረችው ጥቃት አምስት SU-27 ተዋጊ ጄቶችን ማውደሟን የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ተዋጊ ጄቶቹ ላይ ጥቃት የተፈጸመው በኢስካንደር-ኤም ሚሳኤሎች እንደሆነ ያስታወቀችው ሩሲያ፤ በዩክሬን ማዕከላዊ ፖልታቫ ክልል ውስጥ በሚገኘው ማይሮሮድ አየር ማረፊያ ላይ ተጨማሪ ሁለት ጄቶች ላይ ጉዳት ማድረሷን ገልጻለች።

ለውድመት የተዳረጉት ጄቶች ውጊያን ጨምሮ ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎቶች የሚሰጡ እንደነበሩ ተገልጿል።

ዩክሬን በበኩሏ በሩሲያ ስለተፈጸመው የአየር ጥቃት ባትክድም በሩሲያ በኩል የተገለጸው መረጃ መጋነኑን ገልጻለች፡፡

ሆኖም ግን በጥቃቱ ስለደረሰው ጉዳትና ስለጥቃቱ አጠቃላይ ሁኔታ በዩክሬን በኩል የተባለ ነገር የለም ፡፡

የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱ መፈጸሙንና ጉዳት መድረሱን የሚያሳይ የጭስ እና የእሳት ቃጠሎ ምስል መረጃ ያወጣ ሲሆን ጥቃቱ መቼ እንደተፈጸመ ይፋ አለማድረጉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ዩክሬን አሜሪካ ሰራሽ ኤፍ-16 ተዋጊ አውሮፕላኖችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆኗን ተከትሎ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት በመሰንዘር ተዋጊ ጄቶችን ለማውደም ዝግጅት ላይ መሆኗ ተነግሯል፡፡

ሩሲያ በማይሮሮድ አየር ማረፊያ የፈጸመችው ጥቃት ድሮን በመጠቀም የአየር ቅኝት በማድረግ እንደሆነ የገለጸችው ዩክሬን፤ የድሮኖቹን ቅኝት ለመከላከል የሚያስችል መሳሪያ የሌላት መሆኗን አስታውቃለች።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.