Fana: At a Speed of Life!

በአንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚያስከትል ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚያስከትል ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል አመላከተ፡፡

በሚቀጥሉት 10 ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ ስርጭቱ ይበልጥ እንደሚጠናከርም ነው ኢንስቲትዩቱ ያስታወቀው፡፡

በዚህም መሰረት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛው እና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ስፍራዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ ዝናብ ይኖራል ብሏል፡፡

በኦሮሚያ፣ አማራ፣ አዲስ አበባ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሲዳማ ክልሎችም ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ አመላክቷል፡፡

ከሐምሌ 11 እስከ 20 ቀን 2024 ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጸው ኢንስቲትዩቱ÷ ደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ እና መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስፋፋ እና የተጠናከረ የደመና ክምችት ይኖራል ብሏል፡፡

በዚህም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ብዙ ቦታዎችን የሚሸፍን ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል በዚሁ ወቅት የሚኖረው ርጥበት የመኸር ሰብሎችን ለመዝራት እና ማሳን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ተጠቁሟል፡፡

የሚጠበቀው ርጥበት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት በምስራቅ እና ሰሜን ምስራቅ አካባቢ ለሚገኙ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለአረንጓዴ ልምላሜ፣ ለግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል አወንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡

እንዲሁም በአፋር ደናክል፣ በታችኛው አዋሽ፣ በመካከለኛው ገናሌ ዳዋ የግድቦችን የውሃ መጠን በማሻሻል አወንታዊ ሚና አለው ተብሏል፡፡

የሐምሌ ወር ዝናብ ከሚኖረው አወንታዊ ጠቀሜታ ባሻገር በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚያስከትል ከባድ ዝናብ ሊጥል ስለሚችል ህብረተሰቡ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግም ኢንስቲትዩቱ  አሳስቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.