Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ 2 ኢሚግሬሽንን የተመለከቱትን ጨምሮ ሦስት ረቂቅ አዋጆችን አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ኢሚግሬሽንን የተመለከቱ እና በኢትዮጵያና ኩዌት መካከል በስራ ስምሪት ዘርፍ የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ፡፡

የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያና በኩዌት መካከል በስራ ስምሪት ዘርፍ የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ ማብራሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም የመግባቢያ ሰነዱ ዓላማ በሀገራቱ መካከል በስራ ስምሪት መስክ ያለውን ትብብር ለማጠናከርና ህጋዊ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት እንዲሁም በኩዌት የሚገኙ ዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁም ወደ ሁለተኛ ንባብ ተሸጋግሮ አዋጅ ቁጥር 1337/2016 ሆኖ በሙሉ ድምጽ መጽደቁን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንደገና ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁም ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1338/2016 ሆኖ በ4 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡

የኢሚግሬሽን አዋጅን ለማሻሻል የወጣ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ ወ/ሮ እጸገነት ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብም አቅርበዋል፡፡

በዚህም ረቂቅ አዋጁ ጠንካራ የቅድመ ጉዞ መረጃዎችን በማዘጋጀትና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለውን የተዋጣለት የመረጃ ልውውጥ በማሳለጥ ወንጀለኞችና ህገ ወጦች በሀገርና ህዝብ ላይ ጉዳት ሳያደርሱ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ለማድረግ የሚያግዝ ስርአት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁም ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1339/2016 ሆኖ በ2 ተቃውሞ በ4 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.