Fana: At a Speed of Life!

የ2017 የፌደራል መንግሥት በጀት በጥንቃቄ እንዲመራ ምክር ቤቱ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2017 በጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት በጀት ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ እና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ስለማረጋገጡ ጥብቅ ክትትል ይደረጋል አለ፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 35ኛ መደበኛ ስብሰባ በ2017 በጀት አመዳደብና አሥተዳደር ላይ ከገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ጋር ተወያይቷል፡፡

በዚሁ ወቅትም የወጪ ንግድን ከማሳደግ፣ የእዳ ጫናን ከመቀነስ፣ የፕሮጀክቶች አሥተዳደርን ከማሻሻል፣ የዋጋ ንረትን ከማረጋጋት፣ በጀትን በእውቀትና በፋይናንስ አሰራር ከመምራት አኳያ ሚኒስቴሩ ምን ያህል ዝግጁ ነው የሚሉ ጥያቄዎች በምክር ቤት አባላት ተነስተው ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የወጪ ንግድን ከማሳደግ አንጻር በአምራች ኢዱስትሪው ዘርፍ ትኩረት ይደረጋል ያሉት አቶ አህመድ÷ የውጭ እዳ ጫና እንዲቀንስ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡

ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ተቋማቸው ተከታትሎ እንደሚያስፈጽምና ሁሉም ተቋማት የህዝብን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እንደሚያደረግም አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም የደመወዝ ማስተካከያ የሚደረገው ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ መሆኑን በመግለጽ የኑሮ ውድነቱን ለማስተካከል ያላሰለሰ ጥረት እንደሚደረግ አስገንዝበዋል፡፡

የሀብት ብክነትን ከመቆጣጠርና ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አኳያ ከፌደራል ዋና ኦዲተር ጋር በቅርበት እንዲሚሰሩ መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

በየደረጃው ያለው አካል የተመደበውን በጀት በቁጠባና በውጤታማነት የመጠቀም ኃላፊነቱን እንዲወጣም ነው ምክር ቤቱ ያሳሰበው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.