Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ሶማሊያ መፍትሄዎችን ለማመላከት ያለሙ ምክክሮችን ለመቀጠል ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መልካም ጉርብትናን እና ቀጠናዊ መረጋጋትን ከግምት በማስገባት መፍትሄዎችን ለማመላከት ያለሙ ምክክሮችን ለመቀጠል መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቱርክ መንግስት አመቻቺነት የተካሄደውን የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ውይይት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ሚኒስቴሩ በመግለጫው÷ በቱርክ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊዳን ጋባዥነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር አህመድ ሞኤሊም ፊቂ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በአንካራ ተገናኝተው ተወያይተዋል ብሏል፡፡

በቱርክ መንግስት አመቻቺነት የተካሄደው የሁለቱ ሚኒስትሮች ውይይት በሀገራቱ መካከል ላሉ አለመግባባቶች መፍትሄ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ግልፅና ወዳጅነት የተሞላበት የሀሳብ ልውውጥ የተደረገበት እንደነበር ገልጿል፡፡

ሁለቱ ሚኒስትሮች ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን እንደገለጹም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

የቱርክ መንግስት ውይይቱን ለማመቻቸት ስለተጫውተው ገንቢ ሚናም ሚኒስትሮቹ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች መልካም ጉርብትናን እና ቀጠናዊ መረጋጋትን ከግምት በማስገባት መፍትሄዎችን ለማመላከት ያለሙ ምክክሮችን ለመቀጠልም ተስማምተዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ምክክሩን በሀገራቸው ለማስተናገድ የወሰዱትን ተነሳሽነት በማድነቅ ሁለተኛ ዙር ውይይታቸውን ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም በአንካራ ለመቀጠል ተስማምተዋልም ተብሏል፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.