ድሬዳዋና ወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን አስመረቁ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ድሬዳዋና ወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመርቀዋል፡፡
ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ 16ኛ ዙር የተማሪዎች ምረቃ ስነ ስርአዓት ያካሄደ ሲሆን፥ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 513 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።
ከተመራቂዎች መካከል 426ቱ ሴቶች መሆናቸውን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዑባህ አደም (ዶ/ር) ፥ በትምህርት ዘመኑ 122 የምርምር ስራዎች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከ14 ሺህ 800 ተማሪዎች በላይ እያስተማረ መሆኑ ተመላክቷል።
የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ብዙአየሁ ታደለ ለተማሪዎች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
በምረቃ ስነ-ሥርአቱ ዩኒቨርሲቲው የሐረርጌ ባህላዊ ጭፈራ የሆነውን ሸጎዬን በዩኔስኮ ቅርስነት ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል።
በተመሳሳይ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ሲያሰለጥናቸው የነበሩ 2 ሺህ 335 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ያስመረቀው ለ19ኛ ጊዜ ሲሆን ፥ ተመራቂዎቹ በአንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ የሰለጠኑ እንደሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡
በእዮናዳብ አንዱዓለም እና ገላና ተስፋ