Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ወንጀልን ለመከላከል በተደረገ ኦፕሬሽን በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወንጀልን ለመከላከልና ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር በተደረገ ኦፕሬሽን በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሰኔ 5 እስከ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ለ15 ቀናት በተከናወነ ኦፕሬሽን በርካታ የወንጀል ተጠርጣሪዎችንና ኤግዚቢቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን ገልጿል፡፡

በ11ዱ ክፍለ ከተሞች በተደረገ ኦፕሬሽን ከዚህ ቀደም የተሰረቁ 8 የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ማስመለሱንና በተለይ ለወንጀል ፈፃሚዎቹ ሀሰተኛ የተሽከርካሪ ሰሌዳ በተለጣፊ ስቲከር ሲያዘጋጁ የነበሩ ግለሰቦች ከሚጠቀሙበት ኮምፒውተር፣ ላፕቶፕ፣ ፍላሽና ካሜራ ጋር በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ፖሊስ ባደረገው ጠንካራ ሥራ የመኪና እቃዎች በኤግዚቢትነት መያዙንና እንዲሁም ሞተር ብስክሌት በመጠቀም የቅሚያ ወንጀል የፈፀሙ ወንጀለኞች ይዞ ከ700 በላይ ሞባይል ስልኮችን ማስመለሱን አስታውቋል።

የተሰረቀ እቃ በሚገዙ ሕገ-ወጦች ላይ በተወሰደ እርምጃ 108 ላፕቶፖች߹ 6 ኮምፒዩተሮች߹ 11 ካሜራዎች߹ 2 ቴሌቪዥንና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ከተሸሸጉበት ቦታ መያዙን አመላክቷል።

ኮንትሮባንድ፣ ሃሰተኛ ሰነዶችንና መድኃኒቶችን መያዙንም ገልጿል።

ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር በተከናወነ ተግባር 2 ክላሽ ከመሰል 120 ጥይቶች ጋር፣ 67 ልዩ ልዩ ሽጉጦች ከ568 መሰል ጥይቶች ጋር እንዲሁም 2 ኋላ ቀር መሳሪያ ከነተጠርጣሪዎቹ በኦሬሽኑ መያዙን ጠቁሟል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው 24 ኮንደሚኒየም ውስጥ መድኃኒት የማከፋፈልም ሆነ የመሸጥ ፍቃድ የሌላቸውና በሕገ-ወጥ መንገድ መድኃኒት እያዘጋጁ ሲያከፋፍሉ የተገኙ ግለሰቦች መያዛቸውን ገልጿል።

ግለሰቦቹ ያዘጋጇቸውና ለገበያ ሊያቀርቧቸው የነበሩ 169 ብልቃጥ መድኃኒቶች፣ 40 ግሉኮስ፣ በርካታ የመድኃኒት ብልቃጦችና ሕገ-ወጥ ሥራቸውን ለመሥራት የሚገለገሉበት አንድ ማሽን፣ ፕሪንተርና ላፕቶፕ በኤግዚቢትነት መያዙን ፖሊስ አስታውቋል።

በኦፕሬሽኑ ዙሪያ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በሰጡት መግለጫ÷ አዲስ አበባ ፖሊስ ከዚህ ቀደም ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ባከናወነው ኦፕሬሽን አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተደረገ ኦፕሬሽን በወንጀል ተግባራት የተሰማሩ በርካታ ግለሰቦች እጅ ከፍንጅና የወንጀል ፍሬዎችን መነሻ በማድረግ በተደረገ ምርመራ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ግለሰቦች መያዛቸውን ተናግረዋል።

ከወንጀል መከላከል ሥራ ባለፈም ከጸረ-ሰላም ሃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ላይም ሕግን መሰረት በማድረግ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።

ለዚህም የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸው÷አሁንም አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ለፖሊስ መረጃ በመስጠት የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.