Fana: At a Speed of Life!

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞው ዋና ኮሚሽነር ከንፁሃን ግድያ ጋር ተያይዞ በተከሰሱበት ክስ ነጻ ተባሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል ተፈጽሟል ከተባለ የንፁሀን ግድያ ጋር በተያያዘ ክስ የቀረበባቸው የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞ ዋና ኮሚሽነር አቡላ ኦባንግ በተከሰሱበት ክስ ነጻ ተባሉ፡፡

እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ክስ የቀረበባቸው የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ሌሎች የቀድሞ አመራሮችና የልዩ ኃይል አዛዦችን ጨምሮ 12 ተከሳሾች የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

የፍርድ ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ-መንግሥትና በሕገ-መንግሥት ሥርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ክስ አቅርቦባቸው ከነበሩት በክስ መዝገቡ ከተጠቀሱ ተከሳሾች መካከል÷ የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞው ዋና ኮሚሽነር አቡላ ኦባንግ፣ የቀድሞው ም/ኮሚሽነር ቱት ኮር፣ የክልሉ ልዩ ኃይል የቀድሞው ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኮንግ ሬክ እና የክልሉ ልዩ ኃይል የቀድሞው ምክትል አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኡጀዲ ባሬ እና የተለያዩ የፀጥታ አባላትን ጨምሮ አጠቃላይ 15 ተከሳሾች ይገኙበታል።

ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ በጦርነት ጊዜ ንፁሃን ሰዎችን ለመጠበቅ ሲባል የወጣውን የጄኔቫ ቃል ስምምነት የፕሮቶኮል ድንጋጌን በመለተላለፍ እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/ንዑስ አንቀጽ 1 ሀ እና ለ፣ አንቀጽ 35 እና አንቀጽ 270 ስር የተደነገጉ ድንጋጌዎች መተላለፍ የሚል ነበር።

ተከሳሾቹን በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም የሸኔ ሽብር ቡድን እና የጋምቤላ ነጻ አውጪ ፓርቲ (ጋነግ) በጋራ በመሆን በጋምቤላ ከተማ ቀበሌ 03 በፌደራል ፖሊስ ካንፕ እና በክልሉ ልዩ ኃይል እንዲሁም በሌሎች ፀጥታ አካላት ላይ የከፈቱትን ድንገተኛ ተኩስ ተከትሎ በወቅቱ በፀጥታ ኃይሎች የሽብር ቡድኑ ወደ መጣበት እንዲመለስ ከተደረገ በኋላ ማንነታቸው የተለዩ 35 ሰዎች እና ማንነታቸው ያልተለዩ ሌሎች ንፁሃንን መረጃ ሰጥታችኋል በሚል በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ትዛዝ በመስጠትና በግድያው የተሳተፉ አሉ በማለት የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ በክስ ዝርዝሩ ላይ አስፍሮ ነበር።

15ኛ ተከሳሽ ብቻ በሌለበት ጉዳዩ የታየ ሲሆን ቀሪዎቹ ተከሳሾች ግን በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።

ተከሳሾቹ የክስ ዝርዝሩ በችሎት እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት እንደፈጸሙ ጠቅሰው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ ምስክሮች ቀርበው ይሰሙልኝ በማለት አጠቃላይ 37 ምስክሮች እንዳሉት ገልጾ የምስክር ቃል እንዲሰማለት ጠይቆ ነበር።

በፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ሕግ ካስመዘገባቸው ምስክሮች መካከል ከ15 በላይ የሚሆኑ ምስክሮችን የምስክርነት ቃል አዳምጧል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ የምስክርነት ቃል መርምሮ ከተከሳሾች መካከል የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞው ዋና ኮሚሽነር አቡላ ኦባንግ፣ ቀድሞው ም/ኮሚሽነር ቱት ኮር እና የክልሉ ልዩ ኃይል የቀድሞው ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኮንግ ሬክ እና የክልሉ ልዩ ኃይል የቀድሞው ምክትል አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኡጀዲ ባሬን ጨምሮ 13 ተሳሾች በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።

በዚሁ መዝገብ የተካተቱ 7ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ማለትም የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል የቀድሞ አባል ኮ/ል አቶሬ ጉር እና የጋምቤላ ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞ አባል ረ/ሳጅን ቾድ ቤንግን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ በቀረበባቸው ክስ ላይ በቂ ማስረጃ አለመሰማቱን ገልጾ በነጻ እንዲሰናበቱ ብይን መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ ተከላከሉ ያላቸውን ተከሳሾች በተለያዩ ቀናት በየደረጃው ያቀረቡትን የመከላከያ ማስረጃ መርምሯል።

በዚህም ዛሬ በዋለው ችሎት 12 ተከሳሾች የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በበቂ ሁኔታ መከላከል አለመቻላቸው ተጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

በክሱ ላይ በተራ ቁጥር 1 የተከሰሱትን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞው ዋና ኮሚሽነር አቡላ ኦባንግ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከላቸው ተጠቅሶ ነጻ ተብለዋል።

ፍርድ ቤቱም ጥፋተኛ የተባሉ ተከሳሾችንና የዐቃቤ ሕግን የቅጣት አስተያየት ለመጠባበቅ ለሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.