Fana: At a Speed of Life!

የምክክር ኮሚሽኑ አንኳር ተግባራት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አንኳር ተግባራት፡፡

👉ተቋማዊ መስተጋብር በመፍጠር ልምዶችን መቅሰም እና ለምክክር ሂደቱ የሚጠቅሙ ቅድመ ጥናቶችን ማካሄድ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለምክክር ሂደቱ ይጠቅማሉ ብሎ ያመነባቸውን ልምዶች እና ተቋማዊ እውቀቶች ከተለያዩ አካላት ሲቀስም ቆይቷል፡፡

ኮሚሽኑ በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 1265/2014 አንቀፅ 9 (2) መሰረት ከዚህ በፊት በመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የተደረጉ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን እና የተገኙ ውጤቶችን እያጠና፣ በቀጣይ በሚያካሂዳቸው ሀገራዊ ውይይቶች በግብዓትነት መጠቀም እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ አግባብነት ካላቸው ተቋማት ጋር የትብብር ስልት በጋራ ነድፎ ከተቋማቱም ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

በተጨማሪም የሀገራዊ ምክክር ትግበራ ለሀገራችን አዲስ እንደመሆኑ ኮሚሽኑ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በቂ ጊዜን በመውሰድ በሰነድ ተደግፎ ጥናቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ኮሚሽኑ ይህንን ሲያደርግ በሌሎች ሀገራት በምክክር ሂደቶች ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶች በሀገራችን ላይ እንዳይከሰቱ በማሰብ ነው፡፡

👉ሕዝባዊ ውይይቶችን ማድረግ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ በኋላ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሕዝባዊ ውይይቶችንና ትውውቆችን አካሂዷል፡፡

በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ 1265/2014 አንቀፅ 9 (3) መሰረት በተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዱሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ልዩነቶች በጥናት፣ በሕዝባዊ ውይይቶች ወይም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን መንገዶች በመጠቀም መለየት እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ ህዝባዊ ውይይቶችን በሁለት ዙሮች ያከናወነ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ላይ የኮሚሽኑ አባላትና ባለሙያዎች ወደ ሁሉም የክልል ከተሞችና የከተማ መስተዳደሮች በመጓዝ ከህዝብ ጋር ትውውቆችን አድርገዋል፤ ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ዓላማም አስረድተዋል፡፡

በሁለተኛው ዙር ደግሞ በክልል እና በዞን ከተሞች ውስጥ በሀገራዊ ምክክሩ ስነ-ዘዴ (Methodology) ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ገንቢ ውይይቶች ማካሄድ ተችሏል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለድርሻ አካላት ስነ-ዘዴውን እንዲያዳብሩት መንገዶች ተመቻችተዋል፡፡ እነዚህ ውይይቶች በየአካባቢው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ማግኘት ከማስቻሉም ባሻገር ዜጎች በኮሚሽኑ ላይ ያላቸውን አመኔታ እንዲጨምሩ እገዛ አድርጓል፡፡

👉ለአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊዎችን በቡድን እና በግል መለየት

በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ 1265/ 2014 አንቀፅ 9 (5) ላይ ኮሚሽኑ ከመላ ሀገሪቱ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እና አካላትን የሚወክሉ ተሳታፊዎች የሚሳተፉባቸው፣ ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት የሚያስችሉ የተለያዩ የምክክር ስብሰባዎችን በፌዴራል እና በክልሎች ደረጃ እንዲካሄዱ እንደሚያመቻች ሀላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

በዚህም መሰረት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን፣ ባለድርሻ አካላትን እንዲሁም ግለሰቦችን በወረዳ፣ በክልል እና በፌዴራል ደረጃ በመለየት ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት ቁልፍ ተግባር እያከናወነ ይገኛል፡፡

የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በክልሎች (ከተማ መስተዳድሮች) የሚጀመር ቢሆንም ከወረዳ ጀምሮ የተለዩት የሕብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮቻቸውን ወደ ክልሎች (ከተማ መስተዳድሮች) በመላክ በውክልና ሀሳባቸውን የሚያንፀባርቁበት ሂደት ነው፡፡

በዚህ ረገድ ለኮሚሽኑ የልየታ ስራ መሳካት እገዛን ሲያደርጉ የቆዩ የተለያዩ ተባባሪ አካላት ሚና ከፍተኛ እንደነበር እውቅና ሊቸረው ይገባል፡፡

👉የክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የፌዴራል ተቋማት የምክክር ምዕራፍ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን ማካሄድ

ከሕብረተሰብ ተወካዮች መረጣ ቀጥሎ ያለው ተግባር አጀንዳዎችን ከክልል፣ ከፌዴራል እና ከዲያስፖራው ማህበረሰብ በተለያዩ መንገዶች መሰብሰብ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ በሂደቱ እንዲሳተፉ ከለያቸው የማህበረሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎችን ይሰበስባል፡፡ ለሂደቱም መሳካት ኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣን እንዲሁም የቀረፃቸውን መመሪያዎች እና የአሰራር ስርዓቶች ተግባር ላይ ያውላል፡፡

ኮሚሽኑ አጀንዳን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንደሚሰበስብ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ኮሚሽኑ በክልሎች፣በከተማ አስተዳደሮች ፣በፌዴራል እና በዳያስፖራው ማህበረሰብ አጀንዳን ይሰበስባል፡፡

በዚሁ ሂደት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር የተጀመረ ሲሆን በሂደቱ አምስት ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ይህም በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች እየተከናወነ ይቀጥላል፡፡

👉የሀገራዊ ምክክሩን ጉባኤ ማካሄድ

ከሁለም የሀገሪቱ ክፍሎችና ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ግልፅ አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ምክር ቤት በየፈርጁ ተለይተው ከቀረቡ በኃላ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎች ይቀረፃሉ፡፡

ከዚህ በመቀጠል ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ከመላ ሀገሪቱ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እና በላድርሻ አካላት የሚወክሉ ተሳታፊዎች የሚሳተፉባቸው፣ ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚያስችሉ የተለያዩ የምክክር ስብሰባዎችን በአዋጁ መሠረት በፌዴራል እና በክልሎች ደረጃ እንዲካሄዱ ያደርጋል፡፡

በዚህ ሂደት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በእጅጉ አስፈላጊ ስለሚሆን ኮሚሽኑ ሁሉም አካላት ሀሳባቸውን በነፃነት የሚያንሸራሽሩበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

👉የሀገራዊ ምክክሩን ውጤት ማቅረብ

በሀገራዊ ምክክሩ የተገኙ ምክረ ሀሳቦችንና ግኝቶችን ለተለያዩ አካላት ማቅረብ ሌላው ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 1265/ 2014 አንቀፅ 9 (10) የተሰጠው ሀላፊነት ነው፡፡

በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሂደቶች፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን እንዲሁም ምክረ ሃሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ስልት የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈፃሚ አካለት እና ለሌሎች የሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላት እና ለህዝብ ይፋ ያደርጋል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽኑ መንግሥት ከሀገራዊ ውይይቶች የሚገኙ ምክረ ሃሳቦችን በተግባር ላይ ለማዋል እንዲችል ግልፅ እና ተጨባጭ የሆነ ዕቅድ እንዲያዘጋጅ አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል፤ የምክረ ሃሳቦቹን አፈፃፀም ለመከታተል የሚያስችል ሥርዓት ይዘረጋል፡፡

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.