እስራኤል በሊባኖስ ላይ ወታደራዊ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ አስከፊ ጦርነት ይጠብቃታል – ኢራን
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል በሊባኖስ ላይ ወታደራዊ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ከባድ አጸፋዊ እርምጃ ይጠብቃታል ስትል ኢራን አስጠነቀቀች፡፡
ኢራን ይህንን ያለችው እስራኤል በሊባኖስ የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን ይዞታዎችላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጁ ነኝ ማለቷን ተከትሎ ነው፡፡
በተመድ የኢራን ልዩ መልዕክተኛ እንዳሉት÷እስራኤል በሊባኖስ ግዛት ላይ የተሟላ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ የምትጀመር ከሆነ ኢራን ሁሉንም አማራጮች ትጠቀማለች፡፡
ይህም ሊደረጉ በሚችሉ በሁሉም የውጊያ ግንባሮች እስከመሳተፍ እንደሚደርስ ነው የገለጹት፡፡
ሂዝቦላህ የእስራኤል ወታደራዊ ማዕከላትን የሚያሳይ በድሮን የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የሀገራቱ ውጥረት ይበልጥ እየተባባሰ መጥቷል፡፡
አሜሪካ፣ ሩሲያና ብሪታኒያን ጨምሮ ሰባት ሀገራትም በሀገራቱ መካከል እየናረ የመጣውን እሰጣገባ በመስጋት ዜጎቻቸው ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ሃላፊ ማርቲን ግሪፍትስ÷በእስራኤልና ሊባኖስ መካከል ሊፈጠር የሚችል ጦርነት በቀጣናው አስከፊ ውድመት እንደሚያስከትል አስገንዝበዋል፡፡
ይሁን እንጂ የጋዛ ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰው የሀገራቱ የድንበር አካባቢ ግጭት አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው አር ቲ የዘገበው፡፡