Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ቆይታችን አስደሳችና ሀገሪቱም በፈጣን ለውጥ ላይ መሆኗን የተገነዘብንበት ነው – የናይጄሪያ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋቾች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቆይታችን አስደሳች እና ሀገሪቱም በፈጣን ለውጥ ላይ መሆኗን የተገነዘብንበት ነው ሲሉ የናይጄሪያ የቀድሞ ታላላቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ተናገሩ፡፡

የቀድሞ የናይጄሪያ የእግር ኳስ ኮከብ ንዋንኩ ካኑን ጨምሮ የቀድሞ የአህጉሪቱ ታላላቅ ተጫዋቾች በአዲስ አበባ ሸነን አፍሪካ ፌስቲቫል ለመታደም አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል፡፡

በቆይታቸውም ከፌስቲቫሉ በተጨማሪ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

ዛሬ ማለዳ በወዳጅነት ፓርክ በመገኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደረጉ ሲሆን÷በስፍራው ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡

የቀድሞ የናይጄሪያ እግር ኳስ ኮከብ ንዋንኩ ካኑ በዚሁ ጊዜ÷ኢትዮጵያ እጅግ ውብና የሚያስደንቅ ባህል ያላት ሀገር መሆኗን ተናግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ቆይታችን የተደረገልን አቀባበልና እንክብካቤ ቤታችን ያለን ያህል እንዲሰማን አድርጓል ያለው የናይጀሪያ የቀድሞ እግር ኳስ ኮከብ÷በቀጣይም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ እንደሚመጣ ያለውን እምነት ገልጿል፡፡

በቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ራዕይ መሰረት አድርገው እያከናወኗቸው ያሉ የልማት ሥራዎችን ስለመጎብኘታቸውም አንስቷል፡፡

ሌላኛው የናይጄሪያ የቀድሞ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ታሪቦ ዌስት÷በቆይታቸው የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውን ገልጿል፡፡

በቆይታችን ኢትዮጵያውያን በክብርና በፍቅር ተቀብለውናል ያለው ደግሞ ሌላኛው የቀድሞ እግር ኳስ ኮከብ ዳንኤል አሙካቺ ነው፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ካደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ በተጨማሪ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብር መሳተፋቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረበት መግለጹንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.