Fana: At a Speed of Life!

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የምርቃት ድምቀት የሆኑት መንትዮችና እህታቸው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ተመራቂዎቹ መንትዮችና እህታቸው ዛሬ ለተካሄደው የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ መርሐ ግብር ድምቀት ሆነዋል።

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስኮች ካስመረቃቸው 1ሺህ 489 ተማሪዎች መካከል ሁለቱ የኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ተመራቂ መንትዮች እና በህግ ትምህርት የተመረቀችው እህታቸው ለምረቃው ልዩ ድምቀት ሆነዋል።

ልዩ ተመራቂዎቹ ዮናታን ደረጄ፣ ናታን ደረጄ እና እህታቸው የአብስራ ደረጄ ሲሆኑ ውልደትና እድገታቸው በአዲስ አባበ ከተማ ነው።

ሁለቱ የ22 ዓመት ዕድሜ ወንድማማች መንትዮች በተመሳሳይ የኮምፒዩተር ሳይንስ ሙያ መመረቃቸው ደግሞ በብዙዎች ላይ አግራሞትን አጭሯል።

ተማሪ ዮናታን ደረጄ 3 ነጥብ 65፤ ናታን ደረጄ 3 ነጥብ 2 ያመጡ ሲሆን እህታቸው የአብስራ ደግሞ በህግ የትምህርት መስክ 3 ነጥብ 5 በሆነ ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብ ዛሬ ለምረቃ ከመብቃታቸው ባለፈ ለተመራቂዎች ድምቀትም ሆነዋል።

በአንድ ላይ ተምረውና የዩኒቨርሲቲውን መውጫ ፈተና አልፈው በመመረቃችው ደስታቸው ወደር እንደሌለውም ተናግረዋል።

ልዩ ተመራቂዎቹ እንደገለጹት÷ በቀጣይ በሥራው ዓለምም ጠንከረው በመስራት ለሀገር የሚጠቅም ድርጅት የመክፈት ዓላማ ሰንቀዋል።

“ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገብነው በጋራ ጠንክረን በማጥናታችን ነው” ያሉት መንትዮቹ÷ በተመረቁበት ዘርፍ የተሻለ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ወጣት ዮናታን ደረጄ፣ “መንትያ ሆነው አንድ ትምህርት ቤት መማር እድልም ፈተናም” መሆኑን ነው የገለጸው።

እድሉ ስሜትን እኩል መካፈል ሲሆን፤ ፈተናው ደግሞ በመልክ ብዙም ስለማንመሳሰል በትምህርት ቆይታችን ጥያቄ ያበዛብን ነበር ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአብስራ ደረጄ በበኩሏ÷በተለይ ሴት ተማሪዎች ተስፋ ባለመቁረጥ በጥንካሬ ትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ መክራለች።

ተመራቂዎቹ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው ለዚህች ቀንና ለማዕረግ ያበቃቻቸውን እናታቸውንም አመስግነዋል።

እናታቸው ወይዘሮ ደጅይጥኑ ጌታቸው በበኩላቸው÷ ልጆቻቸው አንድ ላይ ለዚህ ማዕረግ በመብቃታቸው ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.