አክሱም እና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመረቁ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አክሱም እና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመርቀዋል፡፡
ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የቡና ሳይንስን ጨምሮ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በቅድመ ምረቃ እና ድህረ ምረቃ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 250 ተማሪዎች አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ 34 ተማሪዎችን በቡና ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ አስተምሮ መቶ በመቶ የመውጫ ፈተናን በማሳለፍ ነው ያስመረቀው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጴጥሮስ ወ/ጊዮርጊስ ( ዶ/ር ) በዚህ ወቅት÷ የቡና ሳይንስ ተመራቂዎች ሀገሪቱ ባላት ዕምቅ የቡና ምርት ላይ የተሻለ ስራን በመስራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን እንዲያግዙ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዩኒቨርሲቲው በቡና ሳይንስ ዘርፍ በድህረ ምረቃ መርሐ ግብር 11 ተማሪዎችን እያሰለጠነ ሲሆን÷ የ ፒኤችዲ መርሐ ግብርን ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዘመኑ የመውጫ ፈተና 1ሺህ 269 ተማሪዎችን አስፈትኖ 1ሺህ 110 ተማሪዎችን በቅድመ ምረቃ መርሐ ግብር ማሳለፍ መቻሉም ተገልጿል።
የዕለቱ የክብር እንግዳና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የምርምር ሥራዎችን እንዲያጠናክርና የአከባቢውን ማህበረሰብ እንዲደግፍ አስገንዝበዋል።
እንዲሁም አክሱም ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎች አስመርቋል፡፡
ተመራቂዎቹ በኮምፒውተር ሳይንስ፣ በሕግ፣ በሕክምና እና ነርሲንግን ጨምሮ በተለያዩ የትምህርት መስኮች የሰለጠኑ መሆናቸው ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገብረኢየሱስ ብርሃነ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው 1ሺህ 50 ተማሪዎች መካከል 190ዎቹ በሁለተኛ ዲግሪ የሰለጠኑ ናቸው።
በፍሬው አለማየሁ