Fana: At a Speed of Life!

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የእቅድ አፈፃፀም ተገመገመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የ2016 በጀት አመት የእቅድ አፈፃፀምን ገምግሟል፡፡

በምክር ቤቱ የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ዑሞድ ኡጁሉ፥ የቋሚ ኮሚቴውን የ2016 የበጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ከክልል ርዕሳነ መስተዳድር ጋር ገምግመዋል፡፡

በዚህም አቶ ዑሞድ፥ አዲሱ የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ በመዋሉ የነበረውን ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየቀረፈ፣ ግልፀኝነት እየፈጠረና የክልሎች የገቢ አቅም እየጨመረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት የነበረውን ክፍተት በጥናት በማስደገፍ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ግልፅ የአሰራር ስርዓት ተዘርግቶለት እየተፈጸመ ይገኛልም ነው ያሉት።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ኃይሉ ኢፋ በበኩላቸው፥ የፌዴራል መሠረተ ልማት ሥርጭት ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በተዘረጋዉ የአሠራር ሥርዓት መሰረት ስለመፈፀሙ ክትትልና ድጋፍ ማድረግና ልዩ ዓላማ ያላቸው የፌዴራል ድጎማዎች ግልፀኝነት ትኩረት ከተደረገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ተጠያቂነትና ዘላቂነት ባለው መልኩ በፍትሃዊነት ለክልሎች መከፋፈሉን ክትትልና ድጋፍ ማድረግና ተያያዥ መረጃዎችን መሰብሰብና ማደራጀት ሌሎች ቋሚ ኮሚቴው ያተኮረባቸው ጉዳዮች እንደነበሩም ነው ያነሱት፡፡

ቋሚ ኮሚቴውም ሪፖርቱና አዲሱ ቀመር ስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ከፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አንጻር የመጣውን ማሻሻያ በጥልቀት ከገመገመ በኋላ የቋሚ ኮሚቴውን ሪፖርት ለምክር ቤቱ መደበኛ ጉባዔ እንዲቀርብ አቅጣጫ አስቀምጧል ነው የተባለው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የ2016 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ እንሚጠበቅ ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.