Fana: At a Speed of Life!

በደሴ ከተማ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች አፈፃፀም አበረታች መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደሴ ከተማ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች አፈጻጸም በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ፡፡

በደሴ ከተማ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውን የገለፁት አቶ ተመስገን÷ የከተማዋን ዕድገት በፍጥነት እውን የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አፈጻጸማቸውም በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ነው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ያሰፈሩት፡፡

የከተማዋ ነዋሪም ለልማቱ ቀኝ እጅ ሆኖ በጋራ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው የከተማዋ ገጽታ በቅርቡ የተሻለ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ዛሬ በደቡብ ወሎ ሐይቅ አጠገብ ያስጀመሩት የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር÷ “የጀመርነውን እንደምናስቀጥል፤ ያስቀጠልነውንም ለፍሬ እንደምናበቃ ማሳያ ነው” ብለዋል።

“ኢትዮጵያ ከቀይ ወደ አረንጓዴ እየተሻገረች ነው። ለዚህም አረንጓዴ ዐሻራ፣ ሀገራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትሕ፣ የተሐድሶ ፕሮግራም ከግጭት የተላቀቀው የአረንጓዴ መንገዳችን ማሳያዎች ናቸው” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም በሐይቅ አጠገብ የገበታ ለትውልድ ውጤት የሆነ ሪዞርት እየተገነባ መሆኑን ገልጸው÷ ሪዞርቱ የሐይቅን ጥንታዊ ታሪክ፣ የተፈጥሮ ጸጋና አስደናቂ ማኅበራዊ መስተጋብር ለዓለም የምናቀርብበት ነው ብለዋል፡፡

በደሴ፣ ሐይቅ እና አካባቢው ለተደረገላቸው የሞቀ አቀባበልም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.