Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ያቀረበው የሰላም ጥሪ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት እንዲፈታ ከህዝብ ተውጣጥቶ የተቋቋመው የሰላም ካውንስል ጥሪ አቀረበ።

ካውንስሉ በጋራ ተሸናፊ ከሚያደርገው የዕርስ በርስ ጦርነት ወደ የጋራ አሸናፊነት ሊያመጣ የሚችል ንግግር መንግስትና ታጥቆ በጫካ ያለው ቡድን ሊመጣ ይገባል ብሏል።

የካውንስሉ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

ከአማራ ክልል የሰላም ካውንስል የተሰጠ መግለጫ፦

“ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም “በሚል በአማራ ከልል ለተፈጠረው ችግር የመፍትሔ ሃሳብ ያመጣሉ ተብለው ከተመረጡ የማህበረተሰብ ከፍሎች ጋር ከሰኔ 17 እስከ 18 ቀን 2016 ዓ.ም በተደረገው የባህር ዳሩ ጉባኤ ለሁለት ቀን መክሯል።

በመጨረሻም ያለ ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ደረጃ፣በየትኛውም ቦታ፣በየትኛውም ሁለቱ ተፋላሚ ሃይሎች ማለትም የመንግስት ሃይሎች እና በጫካ የሚገኙ የፋኖ ወንድሞቻችን ቢያንስ ዘላቂ ተኩስ ለማቆም ንግግርና ድርድር እንዲያደርጉ ጉባኤው ወስኗል።

ለዚህ ሂደትም 15 አባላት ያሉት አመቻች የሰላም ካውንስል መርጧል።

በመሆኑም የተመረጠው የሰላም ካውንስል ሲወያይ ከሰነበተ በኋላ በዛሬው እለት ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል።

የአማራ ክልል ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድሞቹ ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ሃገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከተው ሚና ከፍተኛ ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያን ብቻውን ጠፍጥፎ የሰራት ይመስል አንዳንድ የሀገሩ ልጆች የቀኝ ገዥዎች ሃሳብ በመቀበል የጨቋኝና ተጨቋኝ ትርክት በመፍጠር በተነዛው የሃሰት ፕሮፓጋንዳ፥ ክልሉ አሁን ላለበት ደረጃ አድርሶታል ብለው የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው።

እርግጥ መልኩ መቀየር ካልሆነ በስተቀር እርስ በርስ መዋጋት መፍትሄ ያላመጣ፣ በድህነት ወደኋላ እንድንቀር ያደረገን፣ በሺህ አመታት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበረና ያለ ልንሻገረው ያልቻልን የኋላ ቀርነታችን መገለጫ እንጂ አሁን አዲስ ተፈጥሮ የሚያስደንቀን አይደለም።

ምን አልባት ሊያስደንቀን የሚችለው ከታሪካችን መማር አቅቶ ለዛውም በ21ኛው ከ/ዘመን ወደ ጋርዮሽ ዘመን በሚመለስ አይነት አስቀያሚ የእርስበርስ ጦርነት እያስኬድን መገኘታችን ነው።

ከሺ ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው ሃገር ይዘን መደማመጥ፣መነጋገር እና ወደ ጦርነት ሊወስዱ የሚችሉ ችግሮቻችን በድርድር መፍታት አቅቶን በሴራ ፖለቲካ፣ በሗላ ቀር አመለካከት ወንድም ወንድሙን እያጠፋ ዛሬ ላይ ደርሰናል።

ኢትዮጵያዊያን ብዙ የሚያኮራ አድዋን የመሰለ ታሪክ ያለን ቢሆንም፥ እስከ 21ኛው ክ/ዘመን ይዘነው የዘለቀው የእርስበርስ ግጭት ግን የታሪካችን ስብራት፣መሻገር ያቃተን ሁነት መሆኑ ሁላችንም የኢትዮጵያ ዜጎች ሊቆጨን፣ሊከነክነን እና የመፍትሔ ሃሳብ እንቅልፍ አጥተን ልናስብ ይገባል።

እርግጥ አንዳንድ ምሁራን ጦርነት የሀገረ መንግስት ግንባታ አንዱ አካል አድርገው ቢወስዱትም እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን ፥ ካለን ስሪትና ከመጣንበት መንገድ አንጻር ሲቃኝ በጦርነት እንጨራረሳለን እንጂ አንሸናነፍም።

በአሁኑ ሰዓት የአማራ ህዝብ በዚህ ዘመን ሊፈጠር የማይገባው ግጭት ተፈጥሮ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል አጋጥሞት ይገኛል።

አማራ ክልል ተከስቶ ያለው ግጭት አጠቃላይ ሃገራችን ለጉዳትና ወደ ባሰ ድህነት አረንቋ እየወሰዳት መሆኑ ግልጽ ነው ለዚህ ግጭት መነሻ ምክንያት የአማራ ህዝብ ለዘመናት ሲጠይቃቸው የነበሩ ጥያቄዎች በሰለጠነ ንግግርና ድርድር አለመፈታታቸው፥ ወይም የሚፈቱበት ሂደት ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ አለመቀመጡ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ ።

ዋና ዋናዎቹ የአማራ ክልል ህዝብ ጥያቄዎች ተብለው የተለዩት

1. የተዛባ ትርክትን ማረቅና ማስተካከል

2. የህገመንግስት መሻሻልን

3. የወሰንና የማንነት ጉዳይ

4. ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የውክልና ጉዳይ እና

5. የሀገራችን መዲና የሆነችው የአዲስ አበባ የመልካም አስተዳደር እና የአድሎአዊ አሰራር ችግር አለመቀረፍ

6. በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ህዝብ ጉዳይ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ንጹሃን የአማራ ተወላጆች ለሚደርስባቸው ግድያና መፈናቀል ተጠያቂነት ያለመስፈን ጉዳይ ወዘተ የሚሉ ሁነው ለበርካታ አመታት ትግል ሲደረግባቸው ቆይቷል።

እነዚህ ጥያቄዎች በሃገሪቱ ጥላ ስር በቅንነት በንግግርና በድርድር ሊፈቱ የሚገባቸው እንጂ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚፈታተኑ ጥያቄዎች ይመስል ወደ ጦርነት የሚያስገቡ አልነበረም።

በተለይ በ2008 በኢትዮጵያ አቆጣጠር የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በ2010 በነበረው ለውጥ “የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ሊመለሱ ይችላሉ የሚል ትልቅ ተስፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ለጥያቄዎቹ በቂ ትኩረት ሳይሰጥቸው ቀጥሏል።

አሁንም የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምን ላይ እንዳሉ ምን አይነት የመፍቻ መንገድ እንደተዘጋጀላቸው በተግባር የታዬም ግልጽ ነገር የለም ብሎ ያመነው ህዝቡ ፥ ጥያቄዎች እንዲመለሱለት በሰላማዊ መንገድ ማለትም በህዝባዊ ሰልፍና ስብሰባ እንዲሁም በኮሚቴዎችና የሃገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል።

የክልሉ መንግስትም በህዝቡ ዘንድ ያለው ቅቡልነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሂዷል።

በተጨማሪም ከችግሩ የሚያወጣው ስትራቴጂካልና ታክቲካል መሪ እያጣ እንዲሁም የተደራጀ የፖለቲካ ግንዛቤ ያለው ማህበረሰብ የሚፈጥርለት ምሁር የመከነበት እስኪመስል ድረስ ደርሷል።

በአለፉት አመታት የኢኮኖሚና የማህበራዊ መገለልን የሚቀርፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ ይደረጋል ተብሎ ሲጠበቅ ክልሉ በተለያዩ ወቅታዊ አጀንዳዎች በመወጠርና የደህንነት ስጋት ውስጥ እንዲወድቅ በማድረግ ለከፋ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ተጋልጦ ይገኛል።

በተለይ በቅርቡ የፌደራል መንግስት ከህወሃት ጋር በነበረው ጦርነት ለማስቆም ያደረገው የፕሪቶሪያው ስምምነት በአግባቡ ሳይተገበርና የአማራ ህዝብ የህልውና ስጋት ዋስትና ሳይበጅለት የክልሉ ልዩ ሃይል መፍረስና በጦርነት ተሳትፎ የነበራቸው ታጣቂዎች ለህዝቡ በቂ ግልጸኝነት ሳይፈጠር በከልሉ መንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች በህዝቡ ላይ ጥርጣሬና ስጋት ፈጥረውበታል።

በዚህ ምክንያት የክልሉ የጽጥታ ችግር እየተባባሰ የመጣ ሲሆን ከሀምሌ ወር መጨረሻ 2015 ጀምሮ በከልሉ በነፍጥ የታገዘ ግጭት የተጀመረ ሲሆን ጉዳዩ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመቆጣጠር አስቸግሯል በሚል፥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ አንድ አመት ለተቃረበ ጊዜ የተደረገው ጦርነት ህዝቡ መከራና ምስቅልቅል ሂወት ውስጥ ገብቶ ይገኛል።

በአሁኑ ጊዜ በርካታ የክልሉ አካባቢዎች በመንግስትና የአማራ ህዝብ ጥያቄ ለማስመለስ ጭካ ገባን ባሉ ፋኖዎች መካከል በሚካሄድ በትጥቅ የታገዘ ግጭት ወይም ጦርነት ሳቢያ፥ ብዙ የህዝብ ሃብት ከ12 _13 ቢሊዮን የሚገመት ንብረት ወድሟል፤ንጹሃን ተገድለዋል፤ ከ3.6 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ዉጭ ሆነውል ፤የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ክፉኛ ተጎድቷል ፤የግልና የመንግስት ተቋማት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ባለምቻላቸው ምክንያት የአገልግሎት አሰጣጥ ክፉኛ ተዛብቷል።

ነፍሰጡር እናቶች በአግባቡ የአምቡላንስና የወሊድ አገልግሎት አያገኙም፤እናቶችና ህጻናት ከጦርነት ተሳትፎ ዉጭ የሆኑ የክልሉ ዜጎች ለከፋ የስነ ልቦና ጫና ተዳርገዋል፤እገታ ተስፋፍቷል፤ ዜጎች ያለከልካይ በጠራራ ጸሃይ ይዘረፋሉ፤ይገደላሉ፤ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተስተጓጉለዋል።

ህዝቡ ለሁለት ወገን ግብርና ቀረጥ ይከፍላል እና ሌሎች መሰል ጉዳዮች ግጭቱ ወይም ጦርነቱ ካመጣቸው መዘዞች በጥቂቱ ናቸው።

ይህን ቀውስ በመረዳት ከሰኔ 12 – 13 /2016 አዲስ አበባን ጨምሮ በ8 መድረኮች ችግሩን በትክክል አንስተው የመፍትሄ ሃሳብ ያመጣሉ የተባሉ ከህብረተሰቡ የተውጣጡ ተጽእኖ ፈጣሪ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተደርጓል።

በኋላም በ8ቱ መድረክ በተሳታፊዎች ከተመረጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በባህር ዳር ከተማ ከሰኔ 17 እስከ 18/ 2016 ከሀገሪቱ የጦር ጀኔራሎችና መኮነኖች እንዲሁም የሲቪል አመራሮች ጋር ምክክር ተደርጓል። በመጀመሪያው ዙር በ8ቱ መድረኮች የተነሱ የመፍትሄ ሃሳቦችና በየቀጠናው የተሰጡ የማጠቃለያ መግለጫዎች መለያየትና ቅሬታ የነበረባቸው ቢሆንም፥ በባህርዳሩ ማጠቃለያ መድረክ ግን ከሞላ ጎደል በመድረኩ የተነሳው የመፍትሄ ሃሳብ መግባባትን ፈጥሯል። በዚህ ጉባኤ ጦርነቱ አሸናፊ የሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ስለሆነ በንግግርና በውይይት በድርድር ይፈታ የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል።

ይህ ደግሞ በክልል ደረጃ ሊሆን ይችላል ፤በሀገር ደረጃ ሊሆን ይችላል፤ብቻ በየትኛውም መንገድ ይሁን የአማራን ህዝብ ጥቅም ይዤ ነው የምዋጋው ከሚል ሃይል ጋር ያለቅድመ ሁኔታ ንግግርና ድርድር እንዲደረግ የሚል የጉባኤው ማደማደሚያ የመፍትሄ ሃሳብ ነበር።

በጉባኤው ማጠቃለያ መንግስት ይህ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለው አውዳሚ የእርስ በእርስ ጦርነት በንግግርና በድርድር ለመፍታት ፈቃደኛ ነኝ ነገር ግን ፋኖ አደረጃጀቱና መሪው ብዙ ነው።

ለመደራደር አንድ መሆን አለባቸው በማለቱና የድርድሩ ደረጃ፤ ጊዜና ቦታ ተደራዳሪዎች ተለይተው ሁለቱን ወገኖች እያነጋገረ ለንግግርና ለድርድር ጥረት የሚያደርግ 15 አባላት ያሉት አመቻች የሰላም ካውንስል ተመርጧል።

ካውንስሉ በርካታ ሃላፊነትና ተግባራት ያሉት ሲሆን ከነዚህ መካከል፦

1. ካውንስሉ በሁለቱም ወገኖች እስካልተመረጠ ድረስ አመቻች እንጂ አደራዳሪ አይደለም።

አመቻች ማለት ሁለቱ ወገኖች እኩል ድርድርና ንግግር እንዲቀበሉ አደራዳሪና ተደራዳሪ እንዲመርጡ ቦታና ጊዜ እንዲወስኑ እያለቀ ያለውን ንጹሃን እየተጎዳ ያለው የማህበረሰብ ክፍል ግምት ውስጥ አስገብተው ተኩስ አቁመው እንዲነጋገሩ የማግባባትና የማመቻቸው ስራ ይሰራል ማለት ነው፡፡

2. ካውንስሉ ለየትኛውም ወገን ማዳላት ሳያሳይ በየትኛውም ወገን ጫና ሳይደረግበት ሁለቱም ወገኖች በቅንነት እንዲቀራረቡና እንዲደራደሩ የአመቻችነት ሚናውን ይወጣል።

ከየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነት አያስተናግድም፡በጉባኤው ማደማደሚያ መስረት ስራውን ይወጣል።

ለፌድራል መንግሥት ፣ለአማራ ክልል መንግሥና ለፋኖ ኃይሎች እየተደረገ ያለው የእርስበርስ ጦርነት ነው። ወንድም ከወንድሙ ልጅ ከአባቱ ጋር መገዳደል ነው። በእርስበርስ ጦርነት የሚባባስ እንጂ የሚፈታ ችግር የለም። በሺ አመታት ተሞክሮ መፍትሄ ያላመጣ የእርስበርስ ጦርነት ዛሬ ለዛውም የዘር፣ የብሄርና የሃይማኖት አዝማሚያ ታክሎበት የሚደረግ የእርስበርስ ጦርነት ከመተላለቅ ውጪ አንዳችም መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም።

ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ሰበር ዜና ሊሆን የሚችለው መፍትሄ የማያመጣ የእርስበርስ ጦርነት ማድረጋችን ሳይሆን ከመገዳደል ወጥተን ፖለቲካዊ ልዩነታችን በውይይት፣በመነጋገር፣በመደራደርና በሰጥቶ መቀበል በሚፈታ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ስንገባና ባህል ስናደርግ ያኔ ነው ለኢትዮጵያ ሰበር ዜና መባል ያለበት።

ስለሆነም የወገናችሁ ስቃይ ተረድታችሁ መሸናነፍ በማትችሉበት ጦርነት ከመቆየት ሁለታችሁም ማሸነፍ ወደ ምትችሉበት ንግግርና ድርድር እንድትገቡ አመቻች የሰላም ካውንስሉ አበክሮ ይጠይቃል፣ለማግባባትም ይጥራል።

አንደኛ ለፌደራል መንግስትና ለአማራ ክልል መንግስት መግለጽ የምንፈልገው ይህ የሰላም ካውንስል ሲቋቋም በርቱ፣ ሞክሩ ከጎናችሁ ነን የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ በሌላ ወገን ደግሞ ለሌላ አላማ ወይም ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማስመሰል ካልሆነ በስተቀር እናንተ የምትሉት መንግድ መንግስት የሚቀበለው አይመስለንም ብለው ስጋታቸውን ሲገልጹ ይሰማል።

እርግጥ ሲሆን ከኖረውና እየሆነ ካለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አንጻር የሚጠበቅ አባባል ቢሆንም የህዝባችን ስቃይ አይተን በቅንነት ለምናቀርበው ሃሳብ መንግሥት በቅንነት ተረድቶ ቀጥታ በንግግርና በድርድር የእርስበርስ ጦርነት የምናቆምበት መንገድ ብቻ እንድናተኩር ከመንግስት መታመንን የሰላም ካውንስሉ በትልቁ ይጠብቃል።

ሁለተኛ ለፋኖ ወንድሞቻችንም አጥብቀን ማሳሰብ የምንፈልገው ህዝባችሁ ያለበት ስቃይ ተረድታችሁ አሸናፊና ተሸናፊ በሌለው ጦርነት ከመቀጠል ሁሉንም አሸናፊ ሊያደርግ የሚችለው የድርድር መርህ ተቀብላችሁና ተከትላችሁ እንታገልለታለን የምትሉትን የህዝብ አጀንዳ በንግግርና ድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ እንድትሆኑ እንጠይቃለን።

ለፓለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ለምሁራንና ለማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፤ ለመላው የአማራ ክልል ነዋሪና ለቀሪው የሃገራችን ህዝብ ከፍል፤በውጭ ሀገር ለምትኖሩ የአማራ ክልል እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ስንነግራችሁ ሰምተን ሳይሆን አይተንና መከራና ስቃዩ ግድያው አልፎብን ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ የአማራ ክልል ወገናችሁ በተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት ስቃይ ውስጥ ነው ብለን በ21ኛው ክ/ዘመን አስቀያሚ ጦርነት እያደረግን ያለነው ሰላማዊ ትግል እግር ባለመትከሉና ህዝቡ ከጦርነት ይልቅ ሰላማዊ ትግል እንዲከተል ያልሆነው ሁላችንም የየራሳችን የድክመት ድርሻ አለብን ብለን አለማመናችን ነው።

የእርስ በርስ ጦርነት እየተፈጠረ ያለው በሰላማዊ ትግል የሚያምን ፖለቲካል ማህበረሰብ አለመፈጠሩ ነው ። የፈለገውን ያህል ጦርነት ቢካሄድ ወጣቱ ካለቀ በኋላ አዋጊዎች ወደ ድርድር እንደሚመጡ ከሰሜኑ ጦርነት መማር ያስፈልጋል።

ስለሆነም በእናንተ በኩል ስቃይ ውስጥ ያለውን ማህበረሰብ የእርስ በርስ ጦርነት ማባባስ ሳይሆን ሁለቱ ወገኖች ንግግርና ድርድር የሚያስቀድሙበትን መንገድ ውስጥ እንዲገቡ መገፋፋት ማበረታታትና ማገዝ ትልቁ ድርሻችሁ እንዲሆን እንጠይቃለን።

በመጨረሻም ሰላም የግለስብ ፤የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩ፤የተማሪዎች ፤የሴቶችና የወንዶች የሃይማኖት አባቶች የባለሃቶች፤የአንድ ክልል ህዝብ ፤የመንግስት ሃይሎች፤ጭካ የገቡ የፋኖ አባላት የብቻ ጉዳይ አይደለም።

ሰላም የሁሉም ከሁሉም ነው።ስለሆነም በየደረጃው ጥሪ የተደረገላችሁ አካላት የበኩላችሁን እንድትወጡና ይህ የሰላም ጥሪያችን በአዎንታዊ መልኩ ታይቶ የሀገራችንን ሰላም በጋራ እናምጣ የወንድማማቾች መገዳደል ይብቃ በማለት የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ጥሪውን ያቀርባል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.