Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አግልግሎት መርሃ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አግልግሎት “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በክልሉ በዘንድሮ ክረምት በሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ3 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

በዚህ ወቅት የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አለማየሁ ባውዲ÷ በክረምት በጎ ፈቃድ አግልግሎት በ14 የስራ ዘርፎች ወጣቶችን በማሳተፍ እንደሚከናወንና ከ3 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመስራት መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡

ይህ በጎ ተግባር በወላይታ ዞን 1 ነጥብ 7 ሚሊየን የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና ግማሽ ቢሊየን ብር የመንግስት ወጪን ማዳን የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት አክሊሉ ታደሰ÷ የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የመረዳዳትና አብሮነት ባህልን ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራ ባለው የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎች ትልቅ ድርሻ የሚይዙ ናቸው ብለዋል፡፡

የወጣቶች ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በልምድ ልውውጥ ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባቸውና ወጣቶችም የስራ ባህልን በማሳደግ ለሀገር ብልጽግና የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቀርበዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ÷ በጎ ተግባራት ከአዕምሮ እርካታ በተጨማሪ ከመንግስት ሊወጣ የሚችለውን ብዙ ወጪ የሚያድን ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በማቴዎስ ፈለቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.