Fana: At a Speed of Life!

ግብይት ሳይፈጸም ደረሰኝ በመሸጥ ከ3 ቢሊየን ብር በላይ የታክስ ጉዳት በማድረስ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተከሰሱ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ18 የንግድ ዘርፎች ፈቃድ በመውሰድ ግብይት ሳይፈጸም ደረሰኝ በመሸጥ ከ3 ቢሊየን ብር በላይ የንግድ ትርፍና የተጨማሪ እሴት ታክስ ጉዳት በማድረስ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተከሰሱ።

የፍትሕ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ÷ማቲዮስ ተስፋዬ (በሀሰተኛ ስሙ ሀይሉ አባተ)፣ ቢኒያም ሙሉነህ፣ መኩሪያ አለሙ እና ዮሃንስ አለማየሁ በተባሉ 4 ግለሰቦች ላይ በየተሳትፎ ደረጃቸው ጠቅሶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎትተደራራቢ ክሶችን አቅርቦባቸዋል።

በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 ስር የተመለከተው ድንጋጌ እና የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 በተለይም በዚሁ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር1150/2011 አንቀጽ 49 ንዑስ ቁጥር 3 ስር በተጨማሪ የታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀጽ 116 ፣118 ስር የተመላከቱ ድንጋጌዎችን መተላለፍ የሚሉ ተደራራቢ ክሶችን ነው ዐቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው።

በቀረበው ክስ ላይ 1ኛ ተከሳሽ በየካቲት ወር 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው አዲሱ አስፓልት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሀሰተኛ ስሙ ሀብታሙ ማሞ ለማ ትክክለኛ ስሙ መራዊ ሰለሞን ከበደ የተባለ ግለሰብን ስራ እንስራ በማለት በማሳመን፣ የግለሰቡን ፎቶ አስነስቶ በየካ ክ/ከ ወረዳ 6 ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ቅርጫፍ ጽ/ቤት የሚል ፎቶ ያልተለጠፈበት ሀሰተኛ መታወቂያ አዘጋጅቶ በሀብታሙ ማሞ ለማ ስም በተለያዩ የንግድ ዘርፎች 18 የንግድ ፍቃድ በማውጣት በመጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ ከዚህ ሀሰተኛ መታወቂያ ተዘጋጅቶ ንግድ ፈቃድ በስሙ ከወጣለት ሀብታሙ ማሞ ውክልና የተሰጠው በማስመሰል ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ቅርጫፍ 12 ጽ/ቤት የተሰጠው በማስመሰል ሀሰተኛ የውክልና ሰነድ በማቅረብ ከአንባሰል ንግድ ስራዎች ኃ/የተ/የግል ድርጅት የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ በመውሰድ ደረሰኞችን ለተለያዩ ነጋዴዎች በሽያጭ ሲያቀርብ እንደነበር በክስ ዝርዝሩ ተጠቅሷል።

በዚህም 2 ቢሊየን 627 ሚሊየን 541ሺህ 457 ብር ከ41 ሳንቲም የንግድ ትርፍ እና 1 ቢሊየን 128 ሚሊየን 267 ሺህ 803 ብር ከ03 ሳንቲም የተጨማሪ እሴት ታክስ በአጠቃላይ ከ3 ቢሊየን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ መደረጉ በክሱ ተጠቅሷል።

ሌሎች ተከሳሾችም በየደረጃው የንግድ ትርፍና የተጨማሪ እሴት ታክስ ለማጭበርበር በማሰብ ምንም አይነት የዕቃ ሽያጭ ሳይከናወን የሽያጭ ደረሰኞችን የሚገዙ ነጋዴዎች በማፈላለግና በማገናኘት ደረጃ ተሳትፎ እንዳላቸው ተመላክቷል።

ስለሆነም በዋና ወንጀል አድራጊት፣ ተካፋይ በመሆን ከንግድ ስራ ውጤት ተጠቃሚ ባልሆነ ሰው ስም ንግድ ፈቃድ ማውጣትና ንግድ ስራ መስራት እንዲሁም ግብይት ሳይፈጸም ደረሰኝ መስጠት ወንጀል ተከሰዋል።

ይህ የክስ ዝርዝር ለተከሳሾች እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር በጠየቁት መሰረት ከዐቃቤ ሕግ ጋር ክርክር ተደርጓል።

ፍርድ ቤቱ ክርክሩን መርምሮ ዛሬ በዋለው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ ከቀረበበት የክስ ተደራራቢነትና ከደረሰው ጉዳት አንጻር የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ታዝዟል።

2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ግን ካለቸው ተሳትፎ እና አግኝተዋል ከተባለው ጥቅም አነስተኛ መሆን አንጻር ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍርድ ቤቱ የ450 ሺህ ብር ዋስትና አስይዘው ከእስር እንዲፈቱ እና ከሀገር እንዳይወጡ እግድ እንዲጣል ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

የ4ኛ ተከሳሽን ክስ በተመለከተም ቀደም ሲል በ250 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ እንደተፈቀደለት ተጠቁሟል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ከቀጠሮ በፊት በጽ/ቤት እንዲያቀርቡ በማለት በክስ መቃወሚያውላይ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.