Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በጋራ ለመስራት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በፈረንጆቹ ከ2024 እስከ 2028 በጋራ መስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርማለች።

ስምምነቱን የኢኖቬቨንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ሃይል ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ኋ ሊዩ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ገበያ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ሥርዓት በመፍጠር የበለጸገች ሀገር ለመገንባት እንዲሁም የግል ሴክተሮችን ሚና እና ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡

እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማስጠበቅ፣ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ፣ ምርታማነትን እና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ የፈጠራ ሥነምህዳርን በማጎልበት፣ የሰው ሃይል አቅም ግባታን ለማጠናከር እና በኒውክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቀጣናዊ ትብብርን ለማሳደግ ቁርጠኝነቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው የአፍሪካ ክልል የትብብር ስምምነትና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና መሰረት ሆኖ እንዲቀጥል ተግዳሮቶችን በመለየት የተገኙትን ምቹ ሁኔታዎችና እድሎች በመጠቀም በትብብር መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ኋ ሊዩ በበኩላቸው÷ የተደረገው ስምምነት ላይ በመመስረት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ውጤትን መሰረት ያደረገ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው የኒውክሌር ሳይንስ ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ የማህበራዊና ኢኪኖሚያዊ ጠቀሜታ ላይ ለማዋል ትኩረት አድርጎ በመስራት የትብብር ሥራዎች ወሳኝ ሚና ስላላቸው የሚኖረው ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.