Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ም/ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 37ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ምክር ቤቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

1. በመጀመሪያ ምክር ቤቱ የተወያየው የእንስሳት ጤና እና ደህንነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

ሀገራችን ከእንስሳት አለም አቀፍ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንድትችል ያለንን የእንስሳት ሀብት ማወቅ ፣ የእንስሳት ጤና እና ደህንነትን ማስጠበቅ፣ ከእንስሳት ወደ ሰው፣ ከሰው ወደ እንስሳት ተላላፊ በሽታን መከላከል፣ ድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት በሽታዎች ቁጥጥር ስርዓት በበቂ ሁኔታለመተግበር እና የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የህግ ማእቀፍ ማዘጋጀት አስፈልጓል፡፡

በዚሁም መሰረት የዘርፉን ተዋናዮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችል ግልጽ የእንስሳት ጤና እና ደህንነት ክትትል እና ቁጥጥር ስርአት የሚዘረጋ ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በአዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በኢትዮጵያና በኩዌት መካከል በስራ ስምሪት ዘርፍ የተፈረመውን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ አዋጅ ላይ ነው፡፡

ስምምነቱ በኩዌት በቤት ሰራተኝነት ተሰማርተው የሚገኙ እና በቀጣይም ከአሰሪዎች ጋር የሥራ ውል ውስጥየሚገቡ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች መብታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖር፣ በአገሪቱ የሚገኙ ዜጎቻችን ክብር፣ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው እንዲሁም በሁለቱ መንግስታት መካከል የሁለትዮሽ ግንኙነትን ይበልጥ እንዲጠናከር የሚያግዝ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትእንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

3. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ማሻሻያ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክ ፊርማን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 1072/2010 ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ለአስተዳደሩ እንደ የስልጣናቸው አዋጁን የሚያስፈጽሙበት ዝርዝር ህግ የማውጣት ውክልና በግልፅ ባልሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ህግ የማውጣት ውክልና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ለአስተዳደሩ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የሳይበር ደህንነት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡

ነባሩ ፖሊሲ ለበርካታ አመታት በስራ ላይ የቆየ በመሆኑ የፖሊሲ አቅጣጫ የሚያስፈልጋቸው አዳዲስ ዓለም አለምቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና ሃገራዊ የሳይበር ደህንነትጉዳዮች በዘርፉ ውጤታማነት ላይ ተፅዕኖ የፈጠሩ በመሆኑ፤ የግል እና የመንግስት ቅንጅታዊ እና የትብብር አሰራር በግልጽ ማስቀመጥ በማስፈለጉ እና ሌሎችም ዋና ዋና የትኩረት መስኮችን ያካተተ ግልጽ የአፈፃፀም ክትትልና ግምገማ ዘዴ ያለው ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ምክር ቤቱ በፖሊሲው ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

5. ብሄራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት ጉዳይ ነው፡፡

አርቲፊሺያል ኢንተለጀንስ (AI) በአለም ዓቀፍ ደረጃ ከተዋወቀበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ሀገራት ከጥቃቅን የመዝናኛ እና የመገልገያ ዘዴዎች እስከ ብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ላሉ ቁልፍ ጉዳዮች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡

ሀገራችንም ቴክኖሎጂውን በይበልጥ ለማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አገልግሎት ለማዋልና የሀገር ደህንነትን በማስጠበቅ በዘርፉ ተወዳዳሪ አቅምን ለመፍጠር ተቋም ከማቋቋም ጀምሮ በርካታ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም ቀሪ ስራዎችን መስራት ይጠበቅባታል። የተጀመረውን ለማስቀጠል፣ ዘርፉን ለማሳደግ፣ መንግስት በዘርፉ ሊደርስ የፈለገበትን ግብ ለማመላከት እና ዘርፉ የሚገራበትን አቅጣጫ ለማሳየት በሚረዳ መልኩ ብሄራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱ በፖሊሲው ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶች ታክለውበት ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

6. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በጤና ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ወቅቱ የደረሰበትን የህክምና አገልግሎቶች ታሳቢ ያደረገ፣ የጤና አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል እና የጤና አገልግሎት አስተዳደር ስርዓትን የሚዘረጋ ግልጽ እና ወጥ የሆነ የሕግ ማእቀፍ በስራ ላይ ማዋል አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

7. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው የመድሀኒት ፈንድ እና የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይነው፡፡

ጥራታቸው የተረጋገጠ መሠረታዊ መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋና ዘላቂነት ባለው መልኩ ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ ማቅረብ የሚያስችል ዘመናዊ የመድኃኒት አቅርቦት ሠንሰለት ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

8.በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የጤና ፋይናንስ ስትራቴጂ ላይ ነው፡፡

ሀገራችን በአለምአቀፍ ደረጃ የፈረመችውን የዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካትና የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎትን መሠረት ያደረገ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስፈልገዉን በቂ እና ቀጣይነት ያለው የሀብት አሰባሰብ እና የወጪ አሸፋፈን ስርአት መዘርጋት የሚያስችል የጤና ፋይናንስ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱ በስትራቴጂው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.