ተማሪዎች ውጤታማ ለማድረግ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ ሆነው የሀገር አለኝታ እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
በክልሉ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው የስነ ልቦና ስልጠና ተጠናቋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በወቅቱ እንዳሉት÷ ተማሪዎች ጊዜና ጉልበታቸውን ትምህርት ላይ ብቻ በማዋል ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጋ መሆን ይገባቸዋል።
የክልሉ ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ ሆነው የሀገር አለኝታነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ኩረጃና ስርቆትን በመጠየፍ የራስ ስራ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አቶ ኦርዲን ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡