የኖቤል የሰላም ሽልማቱ የሀገራችንን መልካም ገፅታ ለዓለም ለማሳየት መልካም እድል ይዞ የመጣ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኖቤል የሰላም ሽልማቱ የሀገራችንን መልካም ገፅታ ለዓለም ለማሳየት መልካም እድል ይዞ የመጣ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
የዓለም የኖቤል የሰላም ሎሬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ማለዳ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአቀባበል ስነ ስርዓቱ በኋላ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ይህ ሽልማት እውን እንዲሆን በርካታ እናቶች አብዝተው መጨነቃቸውን ተናግረዋል።
ሽልማቱ የሀገራችንን መልካም ገፅታ ለዓለም ለማሳየት እድል ይዞ መምጣቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በመስማማት እና በመደማመጥ እንዲሁም በሀገር ፍቅር ሀገራችንን ለማሳደግ ይህንን በመልካም አጋጣሚነት ልንጠቀም ይገባልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም፥ የኖቤል ሽልማቱ ለኢትዮጵያና ኤርትራ እንዲሁም ለምስራቅ አፍሪካ በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት እና ስም ያገኘንበት ነው ብለዋል።
ሁሉንም በመወከል በዚያ ስፍራ በመገኘት ለኢትዮጵያ ለኤርትራ ብሎም ለምስራቅ አፍሪካ ያለው እሳቤ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ትኩረት አግኝቶ ሀገራት በዚህም አካባቢ ታሪክ ሊሰራ እንደሚችል ማሰብ እንዲችሉ የማስታወስ ስራ ለመስራት እድል ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።
ሁሉም እንሚገነዘበው የኖቤል ኮሚቴው የሚያውቀውንና የሚገነዘበውን ጠርቶ የሸለመ ቢሆንም፤ ሽልማቱ እውን እንዲሆን ብዙ እናቶች በጓዳ የተጨነቁ፣ ያለቀሱ እና የፀለዩ እንዳሉ ይታወቃልም ነው ያሉት።
በመሆኑም “ሁሉንም በመወከል ሽልማቱን እኔ ብቀበልም፤ ሽልማቱ ለኢትዮጵያና ኤርትራ፣ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ለእኔ እንዲሁም ለተቀሩት ለኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጆች ሁሉ የተሰጠ በመሆኑ እንደ መልካም እድል በመጠቀም ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት እንደ መነሻ አድርጎ መጠቀም መልካም መሆኑንም አንስተዋል።
ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ባስተላለፉት መልእክትም፥ ደሃ ብንሆንም ታሪክ እና ባህል ያለን፣ ለሰላም የምንተጋ ህዝቦች መሆናችንን እንዲሁም ከዚህ ቀደም ያልታወሱ ታሪኮቻችንን እንዲታወሱ እድል አግኝተናል ብለዋል።
“ከዘመናት በፊት የሌሎች ሀገራትን ህዝቦች ተቀብላ ስታስተናግድ የነበረች ሀገር አሁን ታሪኳ እየቀጨጨና እየተረሳ የመጣ ቢሆንም፤ አሁን መልሶ የሚታደስበት እድል በመገኘቱ በተባበረ ክንድ እና በተስማማ ማንነት ሀገራችን ካለችበት ሁኔታ ወደ ብልፅግና እንድትሸጋገር በጋራ ጠዋት ማታ እንድንተጋ እና እንድንጠቀምበት አደራ ማለት እፈልጋለሁ” ብለዋል በመልዕክታቸው።
ኢትዮጵያ ብዙ ጀግኖች ያላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር፥ ነገር ግን ጀግና መወጣጫ መሰላል ከሌለው ጫፍ መድረስ ስለማይችል አንዱ አንዱን ደግፎ ከጫፍ ቢደርስ ትሩፋቱ ለሁሉም አይቀሬ መሆኑን ከሰሞኑ ሽልማት መማር እንደሚቻልም አስታውቀዋል።
የድህነት፣ የረሃብ፣ የጉስቁልና፣ የግጭት እና የጦርነት ታሪኮች እንዲያበቁ እንዲሁም የመተባበር፣ የመደማመጥ፣ የመስማማት እና በጋራ ሆኖ ሀገርንና አካባቢን የመቀየር፤ እኛም እንደ ሌሎቹ መርዳት የምንችል ሀገር እንድንሆን ይህንን አጋጣሚ መጠቀም ተገቢ ነውም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሽልማቱ እውን እንዲሆን ላደረጉት ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ህዝቦች በተለይም ደግሞ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በቅርቡም ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው ድሉን በጋራ እንደሚከያከብሩም ተስፋ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
በሙለታ መንገሻ