Fana: At a Speed of Life!

በበጀት ዓመቱ በሁሉም መስኮች አመርቂ ውጤት ተገኝቷል – አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል በ2016 በጀት ዓመት በሁሉም የልማት መስኮች አመርቂ የአፈፃፀም ውጤት መገኘቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ ገለፁ።

የክልሉ የመስተዳድር ምክር ቤት የክልሉን የዘንድሮ የዕቅድ አፈፃፀም ባለፉት ሶስት ቀናት ገምግሞ፤ የላቀ ዉጤት ላስመዘገቡ ቢሮዎች ዕዉቅና ሰጥቷል።

ይህንን አስመልክቶ አቶ ደስታ ሌዳሞ በሰጡት ማብራሪያ፤ አመራሩ ለዕቅዱ ውጤታማነት ቁርጠኛ አቋም እንዲይዝ በመደረጉና ህዝቡን የሚያሳትፍ የልማት ስትራተጂ በመነደፉ የሚፈለገው ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

የበጀት ብክነት እንዳይከሰት በጥናት ላይ የተመሰረቱ የአሰራር ስልቶች ተዘጋጅተው ተግባራዊ በመደረጋቸው ለውጤታማነቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

የአስተራረስ ዘዴን ማዘመንና በቂ ግብዓቶችን ማቅረብ፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በአርሶ አደሩ ማሳ ተገኝተው ሙያዊ እገዛ እንዲያደርጉ ትኩረት መሰጠቱ ምርታማነትን እንዳሳደገ ጠቁመዋል።

በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የክልሉ ነዋሪዎች በዶሮ እርባታ፣ በወተት ከብት እርባታ፣ በበግና ፍየል እርባታ እንዲሁም መሰል ስራዎች እንዲሰማራ በመደረጉ ህብረተሰቡን በስፋት ወደ አምራችነት ማሸጋገር መቻሉን ገልጸዋል።

የንፁ ውሃ አቅርቦት ሽፋንን ለማሳደግ በተሰራው ስራ ከዚህ በፊት ተጀምረው የነበሩ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ስራዎች እንዲጠናቀቁ መደረጉን ገልጸው፤ የዉሃ ሽፋኑ ከነበረበት 38 በመቶ ወደ 60 በመቶ ከፍ ብሏል ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በመንገድ መሰረተ ልማት፣ በጤና ተደራሽነት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ክልሉ የላቀ አፈጻጸም ማስመዝገቡ እንደተገመገመ አመልክተዋል።

በተገባደደው ዓመት ስራዎቻችንን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ በተሳለጠ የኮሙኒኬሽን ስልትና ስትራተጂ ወደ ህዝባቸውን መድረስ የቻልንበት ዓመት ነዉ ብለዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ዉይይት መደረጉን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በጥናት የለየናቸዉን 8 የለውጥ ኢኒሼቲቮችና 71 ፓኬጆችን የምንተገብርበት ዓመት ስለሆነ አመራሩና ህዝባችን በቂ ዝግጅት እዲያደርግ ሲሉ ማሳሰባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.