Fana: At a Speed of Life!

ረዳት አሰልጣኟ በተመለከቱት የቢጫ ካርድ ምክንያት ከምድቧ 2ኛ ደረጃን ያጣችው ስሎቬኒያ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጀርመን አስተናጋጅነት እየተካሔደ የሚገኘው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ዴንማርክ እና ስሎቪኒያ ተመሳሳይ ነጥብ እና ሪከርዶች እያሏቸው ደረጃ የተለያዩበት መንገድ በዓለም የእግርኳስ ቤተሰብ ዘንድ አግራሞትን ፈጥሯል፡፡

በምድብ ሶስት የተደለደሉት ሁለቱ ሀገራት ሶስት ጨዋታዎችን አድርገው በሶስቱም አቻ ወጥተው ሶስት ነጥቦችን መያዝ ችለዋል፡፡

በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ህግ መሰረት ደረጃቸውን ለመለየት በምድቡ በነበራቸው የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው እና ያስቆጠሯቸው ጎሎች እንደመስፈርት ቢታዩም ሁለቱ ቡድኖች በእርስ በእርስ ግንኙነት 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያዩ ሁለት ጎል አስቆጥረው ሁለት ጎል አስተናግደዋል፡፡

የምድብ 3 መሪ ሆና ካጠናቀቀችው እንግሊዝ በመከተል ሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጠውን ቡድን ለመለየት የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ሌሎች ህጎችን ለመተግበር ተገዷል፡፡

በዚህም መሰረት የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች የዲስፕሊን ሁኔታ ሌላ የመለያ መስፈርት አድርጎ አቅርቧል፡፡

በሚያስገርም ሁኔታ የሁለቱም ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ተመሳሳይ የቢጫ ካርድ ቁጥር አስመዝግበው ነበር፤ ነገር ግን ከተጨዋቾች ውጭ የስሎቬኒያው ረዳት አሰልጣኝ ሚሊቮይ ኖቫኮቪች አንድ ቢጫ ካርድ ማየታቸውን ተከትሎ ዴንማርክ በተሻለ የስነ-ምግባር አፈፃፀም ሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች፡፡

ስሎቬኒያ በረዳት አሰልጣኟ የቢጫ ካርድ ምክንያት ሶስተኛ ደረጃን ብትይዝም በታሪኳ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደጥሎ ማለፉ መግባት ችላለች፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.