በሀሰተኛ ሰነድ ፌሮ ብረቶችን ከቀረጥ ነጻ አስገብቶ ለግል ጥቅም ያዋለው ግለሰብ በጽኑ እስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሆቴል ግንባታ በሚል በሀሰተኛ ሰነድ ፌሮ ብረቶችን ከቀረጥ ነጻ ከውጭ አስገብቶ ለግል ጥቅም ያዋለው ግለሰብ በስድስት ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ዛሬ በዋለው ችሎት በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ቡራዩ ክ/ከተማ ነዋሪ የሆነው ዮሴፍ ዳዊት ሖማ በተባለ ተከሳሽ ላይ የቀረበበት የሙስና ወንጀል ክስና የግራ ቀኝ ማስረጃዎችን መርምሮ የጽኑ እስራት እና የገንዘብ መቀጮ ውሳኔ አስተላልፏል።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀሎች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ በ2008 ዓ.ም የወጣውን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር- 980/2008 በአንቀፅ- 49 ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተደነገገውን ድንጋጌ እና በ2007 ዓ.ም የወጣውን የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 በአንቀፅ 23 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እንዲሁም ንዑስ ቁጥር 2 እና 3 ስር የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከ10 ወራት በፊት ክስ ቀርቦበት ነበር፡፡
ክሱም ተከሳሹ ከሌሎች ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን ለሆቴል ግንባታ በሚል ምክንያት በሀሰተኛ ሰነድ 40 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የፌሮ ብረቶችን ከቀረጥና ታክስ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ምንም አይነት የግንባታ ስራ ሳያከናውን ለግል ጥቅሙ አውሎታል የሚል ነበር።
ተከሳሹ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማቅረብ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ለማውጣት መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋይኤ ሆቴል ኤንድ ሪዞርት ኃላ/የተ/የግ/ማህበር በሚል ስያሜ በውጪና በሀገር ውስጥ ባለሃብት ቅንጅት ለማቋቋም እና እርሱም ድርጅቱን በስራ አስኪያጅነት ለመምራት የኢትዮጵያ አንቨስትመንት ኮሚሽን በመስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ከአዋሽ ባንክ በተጠቀሰ ሂሳብ ቁጥር ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተጻፈና በዋይኤ ሆቴል ኤንድ ሪዞርት ኃላ/የተ/የግ/ ማህበር ስም ሂሳብ ተከፍቶ 7 ሚሊየን 890 ሺህ ብር ገቢ የተደረገ መሆኑን የሚገልፅ የባንክ ሰነድ ማቅረቡን ጠቅሶ በክሱ ላይ ዐቃቤ ሕግ አስፍሯል።
ነገር ግን ተከሳሹ የንግድ ምዝገባውን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለማከናወን ከአዋሽ ባንክ ያቀረባቸው የአቅም ማሳያ የባንክ ሰነዶች ከባንኩ ያልተሰጡና ሀሰተኛ ማስረጃዎች መሆናቸው የተረጋገጠ በመሆኑ፤ በፈፀመው ሀሰተኛ የንግድ ምዝገባ ማስረጃዎችን በማቅረብ በንግድ ምዝገባ መመዝገብ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።
በተለይም በቀረበበት በሁለተኛ ክስ ላይ እንደተጠቀሰው ሀሰተኛ የባንክ ማስረጃዎች በማቅረብ ዋይኤ ሆቴል ኤንድ ሪዞርት ኃላ/የተ/የግ/ማህበር የሚባል የንግድ ድርጅት ካስመዘገበ እና የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወጣ በኋላ በድርጅቱ ስም ባለ ኮኮብ ደረጃ ሆቴል ለማስገንባት ቅድመ ሁኔታዎችን እንደጨረሰና ለግንባታውም 8 ሺህ 500 ቶን ፌሮ ብረት እንደሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የአገልግሎት ፕሮጀክቶች ማበረታቻ ክፍልን መጠየቁ በክሱ ዝርዝር ሰፍሯል።
ብረቱ ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲገባ እንዲፈቀድለት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የቂርቆስ ክ/ከተማ ጽ/ቤት በይዞታ መለያ ቁጥር እና የሴሪ ቁጥር የተጠቀሰበት በመጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ለዋይኤ ሆቴል ኤንድ ሪዞርት ኃላ/የተ/የግ/ማህበር ለተባለ ድርጅት እንደተሰጠ የሚገልፅ የመሬት ይዞታ መብት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እና ከአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም በዋይኤ ሆቴል ኤንድ ሪዞርት ኃላ/የተ/የግ/ማህበር ለተባለ ድርጅት ለሆቴል አገልግሎት ባለ 12 ወለል ሕንጻ ለመገንባት የግንባታ ፈቃድ ምስክር ወረቀት እንደተሰጠው የሚገልፅ ሰነድ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ሰነዶችን በማያያዝ በታህሳስ ወር 2015 ዓ.ም ማመልከቱ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለሆቴሉ ግንባታ ያስፈልጋል በማለት ተከሳሹ ካቀረበው የብረት መጠን ውስጥ በመጀመሪያ ዙር 1 ሺህ 500 ቶን ባጠቃላይ 40 ሚሊየን 665 ሺህ 842 ብር ከ41 ሳንቲም ቀረጥና ታክስ ሊያስከፍል የሚችል ፌሮ ብረት ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲያስገባ እንዲፈቀድለት ለገንዘብ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ መሰረት ተከሳሹ 256 ጥቅል ብረት በድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ ሲሆን ነገር ግን ተከሳሽ የተጠቀሰውን ፌሮ ብረት ከቀረጥና ታክስ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እንዲፈቀድለት ያቀረባቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እና የግንባታ ፈቃድ የምስክር ወረቀት ሀሰተኛ መሆናቸው መረጋገጡን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ዘርዝሯል።
በመሆኑም ተከሳሹ በፈፀመው መንግስታዊ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት ወይም በሀሠተኛ ሰነድ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል፡፡
ተከሳሹ በወቅቱ በተረኛ ችሎት ቀርቦ ክሱ እንዲደርሰው ከተደረገ በኋላ የተከሰሰበት ድንጋጌ ዋስትና የሚያስከለክል ድንጋጌ መሆኑ ተጠቅሶ በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ታዞ የነበረ ሲሆን የተከሰሰበት የወንጀል ድርጊትን አለመፈጸሙን ጠቅሶ የሰጠውን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰነድና የሰው ምስክር አቅርቦ አሰምቷል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ በተከሰሰበት አንደኛው ክስ ከሁለተኛ ክስ ጋር ተጠቃሎ በአንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ንዑስ ቁጥር 2 እና 3 ስር እንዲከላከል ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሹ በተገቢው መከላከል አለመቻሉ ተገልጾ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ በመካከለኛ ደረጃ የተከሳሹን 5 የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን በመያዝ በ6 ዓመት ጽኑ እስራትና በ1 ሺህ 500 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ