አቡበከር ናስር ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር ተለያየ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አጥቂ መስመር ተጫዋቹ አቡበከር ናስር ከደቡብ አፍሪካው ክለብ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር በይፋ ተለያይቷል፡፡
አቡበከር ቀጣይ ማረፊያው የጋናው ክለብ ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡
የ24 ዓመቱ አጥቂ በሰንዳውንስ ያንሰራራል ተብሎ ቢጠበቅም ባጋጠመው የቁርጭምጭሚት ጉዳት ምክንያት በውድድር ዓመቱ መሰለፍ የቻለው ሶስት ጊዜ ብቻ ነው፡፡
የማሜሎዲ ሰንዳውንስ አሰልጣኝ ሩላኒ ሞክዌና አቡበከር ከቡድን ስብሰባቸው ውጭ መሆኑን አስቀድመው የገለፁ ሲሆን ተጫዋቹ በይፋ ከክለቡ ጋር መለያየቱ ተዘግቧል፡፡
ጋና ሶከር ኔትን ጠቅሶ ኪክ ኦፍ እንደዘገበው አቡበከር የጋናውን ክለብ አሳንቲ ኮቶኮ ለመቀላቀል ንግግር መጀመሩ የተገለፀ ሲሆን፤ ክለቡ ለአቡበከር ናስር የሙከራ ጊዜ መስጠቱ ታውቋል፡፡
አቡኪ ከአንድ ሳምንት ሙከራ በኋላ ከክለቡ የፊርማ ውል ሊቀርብለት ይችላል መባሉን ኪክ ኦፍ ስፖርት አስነብቧል፡፡