Fana: At a Speed of Life!

በኬኒያ የተከሰተው ሁከት እንዲረግብ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኬኒያ ፓርላማ ያጸደቀውን የታክስ ሕግ ትከትሎ በሀገሪቱ የተከሰተው ሁከት እና ብጥብጥ እንዲረግብ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጥሪ አቀረቡ፡፡

ሊቀ መንበሩ በዛሬው እለት ባወጡት መግለጫ÷ በኬኒያ የታክስ ሕጉን ምክንያት በማድረግ የተፈጠረው ህዝባዊ ተቃውሞ ህብረቱን እንዳሳሰበው ገልፀው፤ ህብረቱ ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተለው መቆየቱን አንስተዋል፡፡

በህዝባዊ ተቃውሞ የሰው ሕይዎት መጥፋቱን እና ንብረት መውደሙን ጠቅሰው÷ የተከሰተውን ሁከት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት ውይይት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኬኒያን ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ ከሁከት ይልቅ ወደ ንግግር መምጣት አስፈላጊ መሆኑን ሊቀመንበሩ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ÷ በኬኒያ በተከሰተው ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት በደረሰው የሰው ሕይወት ማለፍ እና የንብረት ውድመት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል፡፡

የታክስ ሕጉን መጽደቅ ተከትሎ በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ከሰኔ 18 ጀምሮ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

በህዝባዊ ተቃውሞው ትራንስፖርትን ጨምሮ የቢዝነስ ተቋማት የተዘጉ ሲሆን ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ሞተዋል መባሉን ዘ ስታር ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.