ኢትዮጵያ ከፍልሰት ጋር በተያያዘ ዘርፈ-ብዙ ተግዳሮት እየተጋፈጠች ነው – ም/ ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከፍልሰት ጋር በተያያዘ ዘርፈ-ብዙ ተግዳሮቶችን በመጋፈጥ ላይ እንደምትገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የብሔራዊ ፍልሰት ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የምክር ቤቱን ዓመታዊ የምክክር መድረክ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፤ የሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ተፈጥሯዊና ሕገ-መንግሥታዊ መብት መሆኑን በመግለጽ ይህንን በአግባቡ ማሥተዳደር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በኢትዮጵያም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ከ1 ሚሊየን መሻገሩን አስታውቀው÷ ከፍልሰት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ዘርፈ-ብዙ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጠች ነው ብለዋል፡፡
የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚሄዱ ዜጎችን ከተደራጁ ሕገ-ወጦች ለመታደግ አሠራሮችን መፈተሽና የተቋማትን የቅንጅት ሥራ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ለዚህም ከሌሎች ሀገራት ጋር በጋራ የሚሠሩ የትብብር ተግባራትን በትኩረት መፈጸም ይገባል ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬው መድረኩ የፍልሰት ጉዳዮች ላይ ውይይትና ማብራሪያዎችን አከናውኖ ሀገራዊ የሥራ መመሪያዎችን እንዲሁም አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
በመድረኩ ላይ የክልል ርዕሳነ-መሥተዳድሮች፣ ሚኒስትሮችና የተለያዩ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በፍሬሕይወት ሰፊው